Get Mystery Box with random crypto!

የፍርድ ቤት የብርበራ ማዘዣ አሳዩን ብለው የጠየቁ የሚዲያ ሠራተኞች 8 ቀን በእስር ላይ ሆነው እን | ᴇʟɪᴀꜱ ᴍᴇꜱᴇʀᴇᴛ


የፍርድ ቤት የብርበራ ማዘዣ አሳዩን ብለው የጠየቁ የሚዲያ ሠራተኞች 8 ቀን በእስር ላይ ሆነው እንዲመረመሩ ፍ/ቤት ትዕዛዝ ሰጥቷል።

ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ አስፋው ተከራይቶ የሚሰራበት ስቱዲዮ ፀሃፊ ወ/ሮ መሰረት ታምሩ እና የካሜራ ባለሙያ አቶ አማኑኤል አስፋው በባለፈው ሳምንት ቅዳሜ የካቲት 11 ቀን 2015 ዓ.ም ለእስር መዳረጋቸው የሚታወቅ ነው።

ወ/ሮ መሰረት ታምሩ እና አቶ አማኑኤል አስፋው የቪዲዮ ቀረጻ አገልግሎት ከሚሰጡበት ድርጅት የፍርድ ቤት የብርበራ ማዘዣ ፍቃድ የሌላቸው የመንግስት የጸጥታ ኅይሎች ፍ/ቤት በዋስ እንዲወጣ የፈቀደለትን ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ አስፋ ለፍተሻ እና ብርበራ በሚል ምክንያት ተከራይቶ የሚሰራበት ስቱዲዮ በማስገደድ ብርበራ አካሂደዋል ።

በድርጅቱ የሥራ ቦታ የነበሩ ሠራተኞች ፤ ፖሊስ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ብርበራ አካሂዳለው ማለቱ አግባብ እንዳልሆነ እና የፍርድ  ቤት ማዘዣ ሊደርሳቸው እንደሚገባ ለጸጥታ ኃይሎች ቢገልጹም በማስገደድ ብርበራ በማካሄድ ወ/ሮ መሠረት ታምሩ እንዲሁም አቶ አማኑኤል አስፋው ከላይ በተገለፁት የፀጥታ ሀይሎች ታፍነው ሜክሲኮ በሚገኘው የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ዘርፍ ተወስደው ታስረዋል።

በዛሬው ዕለት በፌደራል የመ/ደ/ፍ/ቤት አራዳ ምድብ ወንጀል ችሎት፤ ከሰዓት በኋላ በዋለው ችሎት ወ/ሮ መሠረት ታምሩ እና አቶ አማኑኤል አስፋው ፤ ከጠበቆቻቸው ጋር ቀርበዋል።

ፖሊስ የጊዜ ቀጠሮ መዝገብ ከፍቶ ለፍርድ ቤት ባቀረበው አቤቱታ ፤ " ተጠርጣሪዎች በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ውስጥ የተፈጠረውን አለመግባባት በመጠቀም ፤ ኢ-መደበኛ አደረጃጀት በመፍጠር ብሔርን ከብሔር በማጋጨት ፣ ሕዝብና መንግስትን ለማጋጨት ፣ ቅስቀሳ በማድረግ ላይ እያሉ በተደረገ ክትትል በቁጥር ሥር ውለዋል። በሰውና በሰነድ ማስረጃ ማጣራት እንድንችል ተጨማሪ 14 ቀናት የምርመራ ማጣራያ የጊዜ ቀጠሮ ይፈቀድልን " በማለት ፖሊስ ለፍ/ቤት ጥያቄውን አቅርቧል ።

የታሳሪዎች ጠበቆች በፖሊስ በኩል ለቀረበው አቤቱታ በሰጡት ምላሽ " ተጠርጣሪዎች የተጠረጠሩበት ጉዳይ የዋስትና መብትን የሚያስከልክል አይደለም ።

እንዲሁም ተጠርጣሪዎች ፖሊስ ሕጋዊ አሰራር እንዲከተል በመጠየቃቸው እንደ አንድ ንቁ ዜጋ የሚያስቆጠር እንጂ ፤ የወንጀል ፍሬ ነገር የሌለው ከመሆኑ ባሻገር በያዛቸው አካል የሚያስመሰግን ድርጊት ከመሆኑ ባለፈ የሚያሳስራቸው አይደለም ።

ከዚህ ጋር ተያይዞ ተጠርጣሪዎች የተያዙት ለምርመራው አጋዥ በሆነ መንገድ ሳይሆን ፤ በሥራ ቦታቸው ላይ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ባሉበት ጊዜ ፖሊስ ለብርበራ መምጣቱን ሲገልጽ የፍርድ ቤት የብርበራ ትዕዛዝ ከያዙ ብርበራ ማድረግ እንደሚችሉ ስለ ተገለጸላቸው ብቻ ይህንን እንደ ሕገወጥ ተግባር በማየት ደንበኞቻችን አስሮ የምርመራ የጊዜ ቀጠሮ መጠየቅ ሕገመንግስታዊም ፣ ሥነ ሥርዓታዊም ባለመሆኑ ደንበኞቻችችን በዋስ መውጣት አለባቸው " በማለት ጠበቆች ለፍ/ቤቱ  ጠይቀዋል ።

ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ ለፖሊስ ተጨማሪ 8 ቀን የምርመራ ጊዜ በመፍቀድ ፤ ለየካቲት 21 ቀን 2015 ዓ.ም ጠዋት 3፡30 ፍርድ ቤቱ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በይድነቃቸው ከበደ

@EliasMeseret