Get Mystery Box with random crypto!

በበዓል ወቅት ሊኖር ሚችለውን የሃይል መቆራረጥ ችግር ለመቀነስ ሲደረግ የቆየው የቅድመ-ዝግጅት ስራ | Ethiopian Electric Utility

በበዓል ወቅት ሊኖር ሚችለውን የሃይል መቆራረጥ ችግር ለመቀነስ ሲደረግ የቆየው የቅድመ-ዝግጅት ስራ ተጠናቀቀ

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በመጪው በትንሳዔ በዓል ወቅት የኃይል መቆራረጥና መዋዥቅ ችግር እንዳይከሰት እና ሲከሰትም አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል የአስቸኳይ ጥገና ግብረ-ሃይል አዋቅሮ የተለያዩ ስራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡

ግብረ-ሃይሉ በተደጋጋሚ የኃይል መቆራረጥና መዋዠቅ ችግር የሚስተዋልባቸውን አካባቢዎች በመለየት የመስመር ፍተሻ፣ በመካከለኛና በዝቅተኛ መስመሮች ላይ የኃይል ጭነት የማመጣጠንና ሌሎች የቅድመ-ጥገና ስራዎችን አከናውኗል፡፡

ተቋሙ በበዓሉ ዋዜማ እና በዕለቱ በሁሉም ማዕከል 24 ሰዓት የአስቸኳይ ጥገና የሚያከናውን ግብረ ሃይል አዋቅሮ ለስራ ዝግጁ አድርጓል፡፡

ይሁን እንጂ በበዓሉ ዋዜማና በዕለቱ የሚኖረው የሃይል አጠቃቀም ከፍተኛ ስለሚሆን የኃይል መቆራረጥና መዋዥቅ ችግር ሊያጋጥም ይችላል፡፡ ስለሆነም ከኤክስፖርትና ሲምንቶ አምራች ኢንዱስትሪዎች ውጪ የሆኑ ከፍተኛ ሃይል ተጠቃሚ ኢንዱስትሪዎች በትንሳዔ በዓል ዋዜማ ከሰአት በኋላ እና በዕለቱ ቀኑን ሙሉ ከዋናው ግሪድ ኤሌክትሪክ ሃይል እንዳይጠቀሙ ተጠይቋል፡፡

ደንበኞችም በቤት ውስጥ የሚገለገሉባቸውን የኤሌክትሪክ ቁሳቁሶች ኃይል ቆጣቢና ለአደጋ የማያጋልጡ መሆናቸውን ማረጋገጥና በቂ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባቸዋል፡፡ በተጨማሪም የኤሌክትሪክ ኃይል ጭነት በማይበዛበት ሰዓት በተለይ ከምሽቱ 3፡00 እስከ ንጋቱ 11፡00 ባሉት ጊዚያት ቢጠቀሙ የተሻለ የኤሌክትሪክ ኃይል ከማግኘት ባለፈ ሊኖር የሚችለውን የሃይል መቆራረጥ ችግር ለመቀነስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡
የቅድመ ክፍያ ተጠቃሚ ደንበኞችም በዓሉ ሲደርስ የሚኖረውን አላስፈላጊ እንግልት ለማስቀረት እንዲችሉ ከወዲሁ የሚበቃቸውን ያህል የኤሌክትሪክ ኃይል አስቀድመው እንዲገዙ /ካርድ እንዲሞሉ እናሳስባለን፡፡

የኤሌክትሪክ ኃይል በሚቋረጥበት ጊዜ የጥገና ስራ ለማከናወን የተቋማችንን መታወቂያ የያዙ የቴክኒክ ባለሞያዎቻችን በተለያዩ አካባቢዎች ለስራ ጉዳይ እንደሚንቀሳቀሱ የሚታወቅ ሲሆን የጥገና ሰራተኞች በመምሰል መሠረተ-ልማቱ ላይ ስርቆትና ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ አካላት ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በመሆኑም ህብረተሰቡ ይህንን ተገንዝቦ የኤሌክትሪክ ማሰራጫ መስመሮችን በመጠበቅ እንዲተባበርና እኩይ ተግባራት ሲፈፀሙ ሲመለከትም ለሚመለከተው የህግ አካላትና ለተቋሙ ማሳወቅ ይገባዋል፡፡

በመጨረሻም ማንኛወንም አስተያየትና ጥቆማ ለመስጠት ወደ አቅራቢያ የአገልግሎት መስጫ ማዕከል በአካል በመሄድ ወይም ወደ 905 ነፃ የጥሪ ማዕከል መደወል ማሳወቅ እንደሚያስፈልግ እንጠቁማለን፡፡

#የኢትዮጵያኤሌክትሪክአገልግሎት