Get Mystery Box with random crypto!

በማሻሻያ ፕሮጀክቱ 150 ሺ አዲስ ደንበኞች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ይሆናሉ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ | Ethiopian Electric Utility

በማሻሻያ ፕሮጀክቱ 150 ሺ አዲስ ደንበኞች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ይሆናሉ

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በአገሪቱ በሚገኙ ስድስት ከተሞች በሚያከናውነው የኤሌክትሪክ ማሰራጫ መስመሮች መልሶ ግንባታና አቅም ማሳደግ ፕሮጀክት 150 ሺ አዲስ ደንበኞችን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ፡፡

እነዚህ አዲስ ደንበኞች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ የሚሆኑት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ካለፈው ዓመት ጀምሮ በወላይታ ሶዶ፣ ሐረር፣ ሻሸመኔ፣ ደብረ ማርቆስ፣ ጎንደርና ኮምቦልቻ ከተሞች እያከናወነ በሚገኘው የመስመሮች መልሶ ግንባታና አቅም ማሳደግ ፕሮጀክት አማካኝነት ነው፡፡

የአገልግሎቱ ተጠቃሚ የሚሆኑት የህብረተሰብ ክፍሎች የኤሌክትሪክ መስመር በአካባቢያቸው ተዘርግቶ ነገር ግን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ያልሆኑ እንዲሁም ከተዘረጋው መሰረተ ልማት እስከ 2.5 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኙትን የሚያካትት ነው፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በከተሞች ያለውን የኃይል አቅርቦት አስተማማኝና ጥራት ያለው ለማድረግና የኃይል መቆራረጥ ለመቀነስ ያረጁ የኤሌክትሪክ መስመሮችን መልሶ ለመገንባትና ለማሻሻል የሚያስችሉ ፕሮጀክቶችን በከፍተኛ ወጪ ተግባራዊ እደረገ ይገኛል፡፡

ከነዚህ መካከል የስድስቱ ከተሞች ፕሮጀክት አንዱ ሲሆን እስካለፈው ጥር ወር ድረስ አፈፃፀሙ 74.35 በመቶ ደርሷል፡፡

በአሁኑ ወቅት በፕሮጀክቱ የኮንክሪት ምሰሶ ተከላ፣ የዝቅተኛና የመካከለኛ መስመር ዝርጋታ፣ መስመር ላይ የሚገጠሙ መሳሪያዎችን ማሰር፣ ቀሪ ግብዓቶችን ወደ ግንባታ ቦታዎች ማጓጓዝ፣ የተመረቱ ግብዓቶች ፍተሻ ማከናወን የመሳሰሉ ስራዎች በመከናወን ላይ ይገኛሉ፡፡

#የኢትዮጵያኤሌክትሪክአገልግሎት

ወቅታዊና ትኩስ መረጃዎች ወዲያውኑ እንዲደርሳችሁ ይህንን ቴሌግራም ቻናል ይጎብኙ፡ t.me/eeuethiopia