Get Mystery Box with random crypto!

የማዕከላዊ እቃ ግምጃ ቤቱ ንብረት አያያዝ እየተሻሻለ መምጣቱ ተገለፀ ***************** | Ethiopian Electric Utility

የማዕከላዊ እቃ ግምጃ ቤቱ ንብረት አያያዝ እየተሻሻለ መምጣቱ ተገለፀ
*****************
ላለፉት ስድሳ ዓመታት ሲያገለግል የቆየው የጎፋ ማዕከላዊ እቃ ግምጃ ቤት የንብረት አያያዝ በአሁኑ ወቅት ለውጥ ማሳየቱን የሎጅስቲክስና ዌርሃውስ ኃላፊ ቢኒያም ገ/እግዚአብሔር ገልፀዋል፡፡

አዲስ የሚገቡና የነበሩ፣ ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉ፣የአገልግሎት ዘመናቸው ያለፈባቸው፣ እና ጥቅም ላይ ውለው ተመላሸ የሆኑ ንብረቶችን ለይቶ በማስቀመጥ የንብረት አያያዙን ላይ ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮችን መቀነስ ተችሏል ብለዋል፡፡

በተቋሙ የግዢ፣ ሎጅስቲክስ፣ ንብረትና ፋሲሊቲ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ኢሳያስ ደንድር በበኩላቸው ከዚህ ቀደም ይስተዋሉ የነበሩ በእቃ ግምጃ ቤት የሚቀመጡ ዝቅተኛ መጠን ያላቸው መጠባበቂያ ግብዓቶች አያያዝ ክፍተቶችን በማረምና የክትትል ስራዎችን በስፋት በመስራት ማሻሻል እንደተቻለ ገልፀዋል፡፡

በግምጃ ቤቱ አገልግሎት የማይሰጡ ንብረቶችን በማስወገድ፣ ጠቃሚዎቹንም በስርዓት በመደርደር፣ ቅጥሩን በማፅዳት፣ የተለያየ ስፋት ያላቸው መጋዘኖችን በመገንባት ከመጋዘን እጥረትና ከአቀማመጥ ችግር ጋር ተያይዞ የሚፈጠር የንብረት ብክነትን መከላከል መቻሉን አቶ ኢሳያስ ጨምረው አብራርተዋል፡፡

የንብረት ስርጭትን በተመለከተ ክልሎች በራስ አቅም ግብዓት የመግዛት ስልጣን ያላቸው መሆኑን የገለፁት አቶ ቢኒያም፤ከጎፋ ማዕከላዊ እቃ ግምጃ ቤት ለሚሰራጩ ንብረቶች እንደተቋም ተግባራዊ በተደረገው የኢ.አር.ፒ የአሰራር ስርዓት መሠረት ስርጭቱ በግልፅ እየተፈፀመ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ይህም በግምጃ ቤቱ ያሉ ንብረቶችን እና ወጪና ገቢን በቀላሉ ለመቆጣጠር ያስቻለ ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም በነበረው የወረቀት አሰራር የሚመጣ የሰነድና የመረጃ መጥፋትን አስቀርቷል ብለዋል፡፡

ተቋሙ የማይጠቀምባቸው ንብረቶች በእርዳታ ወይም በሽያጭ እየተወገዱ መሆኑን የጠቆሙት ኃላፊው፤ ባለፈው በጀት ዓመት በክልሎችና በኮርፖሬት ደረጃ ከተደረገ የንብረት ማስወገድ በአጠቃላይ 1 መቶ 11 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር ገቢ ተገኝቷል ብለዋል፡፡

እንደ አቶ ቢኒያም ገለፃ በአይነት ከ15 ሺህ በላይ ንብረቶችን በግምጃ ቤቱ የሚገኙ ሲሆን፤ ከነዚህ ውስጥ አገልግሎት መስጠት የሚችሉት ወደ 3 ሺህ የሚጠጉ ብቻ ናቸው፡፡

በመሆኑም የ2015 በጀት ዓመት አገልግሎት የማይሰጡ የተጠራቀሙ ንብረቶች ተወግደው የሚያልቁበት የመጨረሻ ዓመት ይሆናል ሲሉ አያይዘው ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል የንብረት ደህንነትን ከማስጠበቅ አንፃር በቅጥሩ ከሚገኙ 24 የጥበቃ ማማዎች በተጨማሪ በቅጥር ግቢው የተገጠሙ የደህንነት ካሜራዎች ስርቆትን አስቀድሞ ለመከላከልና ድርጊቱ ከተፈፀመ በኃላም ወንጀለኛውን ተጠያቂ ለማድረግ ጉልህ አስተዋፅኦ አለው ብለዋል፡፡

በመጨረሻም ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የተቋሙን ንብረት በኃላፊነት እንዲጠብቅ አቶ ቢኒያም አሳስበዋል፡፡

#የኢትዮጵያኤሌክትሪክአገልግሎት

ወቅታዊና ትኩስ የተቋማችን መረጃዎች ወዲያውኑ እንዲደርሳችሁ እነዚህን የትስስር ገፆቻችንን ይወዳጁ፡-

ፌስቡክ፡ https://www.facebook.com/EEUOfficial/
ቲዊተር፡ https://twitter.com/EEUEthiopia
ቴሌግራም፡ t.me/eeuethiopia
ዩቱዩብ: https://www.youtube.com/c/EthiopianElectricUtility
ድረ-ገፅ፡ http://www.eeu.gov.et