Get Mystery Box with random crypto!

ወርሃዊ የኤሌክትሪክ ፍጆታ ሂሳብ እንዴት በቀላሉ ማወቅ ይቻላል? ************* የኢትዮጵያ | Ethiopian Electric Utility

ወርሃዊ የኤሌክትሪክ ፍጆታ ሂሳብ እንዴት በቀላሉ ማወቅ ይቻላል?
*************
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በአሁን ወቅት ከ3 ነጥብ 32 ሚሊዮን በላይ የድህረ ክፍያ ተጠቃሚ ደንበኞች አሉት፡፡ ከእነዚህ ደንበኞቹ መካከል በርካቶቹ የተጠቀሙበትን ወርሃዊ የኤሌክትሪክ ፍጆታ ሂሳብ እንዴት እንደሚሰላ ባለማወቃቸው የተጋነነ የፍጆታ ሂሳብ የተጠየቁ እየመሰላቸው ተደጋጋሚ ቅሬታ ሲያቀርቡ ይስተዋላል፡፡

ይሁን እንጂ ቅሬታው የሚነሳው ደንበኞች የተጋነነ ሂሳብ እንዲከፍሉ በመደረጉ ሳይሆን የኤሌክትሪክ ኃይልን በአግባቡና በቁጠባ ባለመጠቀም እንዲሁም የፍጆታ ሂሳብ እንዴት መሰላት እንዳለበት በቂ መረጃ ካለመያዝ የመነጨ ነው፡፡

ስለሆነም የድህረ ክፍያ ተጠቃሚ ደንበኞች በመኖሪያ ቤታቸው የሚጠቀሙባቸውን የኤሌክትሪክ ቁሳቁሶች የኃይል መጠን መነሻ በማድረግ ምንያህል ኪ.ዋ.ሰ እንደተጠቀሙና ምን ያህል ወርሃዊ የፍጆታ ሂሳብ እንደሚከፍሉ መረዳት ይችላሉ፡፡

ይህንንም በቀላሉ ለመረዳት እንዲያስችል የአንድ የመኖሪያ ቤት ድህረ-ክፍያ ተጠቃሚ ደንበኛ የሆነ ሰው ወርሃዊ የኤሌክትሪክ ፍጆታ ስሌቱ በሚቀጠለው ምሳሌ እናስቀምጠው፡-

• አንድ ደንበኛ በመኖሪያ ቤቱ 4 ባለ 60 ዋት አምፖሎች በቀን ለ6 ሰዓት በወር ለ30 ቀናት ቢያበራ፣

• 3000 ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የሚጠቀም የእንጀራ ምጣድ በቀን ለ2 ሰዓት በወር ለ10 ቀናት ቢጠቀም፣

• 1000 ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የሚጠቀም ምድጃ በቀን ለ5 ሰዓት በወር ለ30 ቀናት ቢጠቀም፣

እና ይህ ግለሰብ ሌሎች የኤሌክትሪክ መገልገያ ቁሳቁሶች ሳይጨምር በወር ውስጥ ምን ያህል ኪ.ዋ.ሰ እንደተጠቀመና ምን ያህል የፍጆታ ሂሳብ እንደሚከፍል ለማወቅ የተጠቀመበትን የኤሌክትሪክ ኃይል በመደመር ወደ ኪ.ዋ.ሰ መቀየር ይጠበቅበታል፡፡

በዚህም መሰረት
 4 አምፑል X 60 ዋት x 6 ሰዓት x 30 ቀናት = 43,200 ዋት.ሰ፣
 3000 ዋት ኤሌክትሪክ የኃይል የሚጠቀም ምጣድ x 2 ሰዓት x 10 ቀናት = 60,000 ዋት.ሰ፣

 1000 ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የሚጠቀም ምድጃ x 5 ሰዓት x ለ30 ቀናት = 150,000 ዋት.ሰ፣

ሶስቱም ሲጠቃለሉ 43,200 ዋት.ሰ + 60,000 ዋት.ሰ + 150,000 ዋት.ሰ = 253,200 ዋት.ሰ ይሆናል፡፡ ይህም ወደ ኪሎ ዋት ሰዓት መቀየር አለበት፡፡
1 ኪሎ ዋት ሰዓት = 1000 ዋት ሰዓት በመሆኑ፤ 253,200 ዋት ሰዓት = 253.2 ኪሎ ዋት ሰዓት ይሆናል፡፡

የመኖሪያ ቤት የታሪፍ ስሌት 7 ደረጃዎች ያሉት ሲሆን፤ አንድ የመኖሪያ ቤት ደንበኛ በወር የተጠቀመበት የኤሌክትሪክ ኃይል በሚያርፍበት የታሪፍ እርክን ተባዝቶ እንዲከፍል ይደረጋል፡፡

በዚህ ስሌት መሰረት ከላይ በምሳሌው የጠቀስነው ደንበኛ በወር 253.2 ኪ.ዋ.ሰ የኤሌክትሪክ ኃይል የተጠቀመ በመሆኑ በቀጥታ 4ኛው እርከን ላይ ያርፋል፤ በመሆኑም በ2.0000 ብር ይባዛል፡፡

በዚህ መሰረት 253.2 ኪ.ዋ.ሰ x 2.0000 ብር= 506.4 ብር ይመጣል፡፡
የአገልግሎት ክፍያ ብር 42 ሲደመርበት በአጠቃላይ ይህ ደንበኛ ወርሃዊ የፍጆታ ሂሳቡ 548 ብር ከ 4 ሳንቲም ይሆናል ማለት ነው፡፡

ስለሆነም ደንበኞች የምትጠቀሙባቸው የኤሌክትሪክ ቁሳቁሶች የሚጠቀሙትን የኃይል መጠናቸው በመለየትና በቀን ውስጥ የምትገለገሉበት ጊዜ በማወቅ ወርሃዊ ፍጆታችሁን በቀላሉ መረዳት ትችላላችሁ፡፡

ገንዘባችሁ ይበልጥ ለመቆጠብ ደግሞ በቤት ውስጥ ኃይል ቆጣቢ የኤሌክትሪክ መገልገያ ቁሳቁሶቹ መጠቀም፤ የአጠቃቀም ሰዓት መለየትና የኃይል ጭነት በማይበዛበት ሰዓት መጠቀም ያስፈልጋል፡፡

ማንኛውንም የቤት ውስጥ የኤሌክትሮኒክስ መገልገያዎች ሲገዙ የኃይል ቆጣቢ መሆናቸዉን ማረጋገጥ፣ ረዥም ጊዜ ያገለገሉ የቤት ውስጥ የኤሌክትሮኒክስ መገልገያዎችን በአዲስ መቀየር፣ ሁሉንም የኤሌክትሪክ ዕቃዎች አገልግሎት በማይሰጡበት ጊዜ ማጥፋትና ሶኬቶችንም መንቀል ተገቢ ነው፡፡

#የኢትዮጵያኤሌክትሪክአገልግሎት

ወቅታዊና ትኩስ የተቋማችን መረጃዎች ወዲያውኑ እንዲደርሳችሁ እነዚህን የትስስር ገፆቻችንን ይወዳጁ፡-

ፌስቡክ፡ https://www.facebook.com/EEUOfficial/
ቲዊተር፡ https://twitter.com/EEUEthiopia
ቴሌግራም፡ t.me/eeuethiopia
ዩቱዩብ: https://www.youtube.com/c/EthiopianElectricUtility
ድረ-ገፅ፡ http://www.eeu.gov.et