Get Mystery Box with random crypto!

ከ200 በላይ የገጠር ከተሞችና መንደሮች የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ሆኑ ******************** | Ethiopian Electric Utility

ከ200 በላይ የገጠር ከተሞችና መንደሮች የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ሆኑ
*************************
የፕሮጀክቶች ፖርትፎሊዮ ማኔጅመንት ዳይሬክቶሬት በአገር አቀፍ ኤሌክትሪክ አቅረቦት ፕሮግራም ጽ/ቤት በ2014 በጀት አመት የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን እውን ለማድረግ በሰራው ስራ 204 የገጠር ከተሞችና መንደሮች የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ማድረጉን አስታውቋል፡፡

ይህ የተገለፀው ዛሬ ሐምሌ 5 ቀን 2014 ዓ.ም ቢሾፍቱ ከተማ በሚገኘው ፒራሚድ ሆቴልና ሪዞርት ባካሄደው የ2014 በጀት አመት ዕቅድ አፈጻፀም ግምገማና የ2015 በጀት አመት ዕቅድ ውይይት ላይ ነው፡፡

የፕሮጀክቶች ፖርትፎሊዮ ማኔጅመንት ዳይሬክቶሬት በበጀት አመቱ 2 መቶ 50 ሺህ አዳዲስ ደንበኞችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ አቅዶ 68 ሺህ 3 መቶ 64 ደንበኞችን የኃይል ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ከቀረቡው ሪፖርት መረዳት ተችሏል፡፡

ለደንበኞች ቆጣሪ በማገናኘት ለመሰብሰብ ካቀደው 253 ሚሊዮን 673 ሺህ 9 መቶ 95 ነጥብ ከ 85 ሳንቲም ውስጥ 73 ሚሊዮን 413 ሺህ 7 መቶ 75 ከ22 ሳንቲም መሰብሰብ ችሏል፡፡

ከመስመር ዝርጋታ አንጻር 4 ሺህ 2 መቶ 50 ኪ.ሜ የመካከለኛ መስመር ለመዘርጋት አቅዶ 2 ሺህ 4 መቶ 96.69 ኪ.ሜ በመዘርጋት የዕቅዱን 58 ነጥብ 75 በመቶ መፈፀም ችሏል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም 2 ሺህ 52 ኪ.ሜ የዝቅተኛ መስመር ለመዘርጋት አቅዶ 1 ሺህ 9 መቶ 23.78 ኪ.ሜ በመዘርጋት የዕቅዱን 93 ነጥብ 75 በመቶ አፈጻጸም ያስመዘገበ ሲሆን 1 ሺህ 66 ትራንስፎርመሮች ለመትከል አቅዶ 5 መቶ 55 ትራንስፎርመሮችን በመትከል የዕቅዱን 52 በመቶ መፈፀም ችሏል፡፡

ከዋናው የኤሌክትሪክ መረብ ርቀው የሚገኙ የገጠር መንደሮችንና ከተሞችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ የሚገኘው የ12 የፀሃይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ሳይቶች ውስጥ 10ሩ ተጠናቀው አገልግሎት እየሰጡ መሆኑንና ቀሪዎቹ በሂደት ላይ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

ከአፍሪካ ልማት ባንክ በተገኘ የገንዘብ ብድር እየተከናወነ የሚገነው የ25 ከተሞች የሶላር ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት አካል የሆኑት የዳራቶሌ፣ የሂግሎሌ፣ ቦኮሎማዮ እና የእርጎየ ሳይቶች ላይ የግንባታ ስራ መጀመሩና በቀሪ ሳይቶች ላይ የዲዛይን፣ የውጭ እቃዎችን የማስገባት ስራ እየተከናወነ ይገኛል፡፡

ከዓለም ባንክ በተገኘ 400 ሚሊዮን ዶላር ከ200 በላይ የገጠር መንደሮችና ቀበሌዎችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ ተግራዊ እየተደረገ የሚገኘው የአዴል (ADELE) ፕሮጀክት በመጀመሪያ ዙር የዳሰሳ ጥናት ከተካሄደባቸው 114 መንደሮች ውስጥ 83 ከተሞች አዋጪ መሆናቸውን ተረጋግጧል፡፡

የፀሃይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች በአካባቢው የሚገኙ የጤና፣ የትምህርት፣ የውሃ ተቋማት፣ የእርሻ ማዕከላት፣ ወፍጮ ቤቶች እና ሌሎችም አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ማድረግ የህብረረሰቡን የኑሮ ሁኔታ በማሻሻል ላይ እንደሚገኙ ከቀረበው ሪፖርት መረዳት ተችሏል፡፡

በመጨረሻም በሃገሪቱ የሚፈጠሩ የፀጥታ ችግሮች፣ የኮንትራክተሮች የመፈፀም አቅም ውስንነት፣ ከወሰን ማስከበር ጋር የተያያዙ ችግሮች፣ የሲምንቶ ዋጋ ንረት፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት እና መሰል ችግሮች የተጀመረውን ኤሌክትሪክ የማዳረስ ስራ በተፈለገው መጠን እንዳይከናወን እንቅፋት መሆናቸው ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የተጣለበትን ኤሌክትሪክ የማዳረስ ሃገራዊ ሃላፊነት እውን ለማድረግ በብሄራዊ ኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም እ.ኤ.አ በ2025 ከዋናው ግሪድ 65 በመቶ እንዲሁም በአማራጭ የኃይል ምንጮች 35 በመቶ የሚሆነውን ህብረተሰብ የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ ከፍተኛ ርብርብ እያደረገ መሆኑ ይታወቀል፡፡

#የኢትዮጵያኤሌክትሪክአገልግሎት

ወቅታዊና ትኩስ የተቋማችን መረጃዎች ወዲያውኑ እንዲደርሳችሁ እነዚህን የትስስር ገፆቻችንን ይወዳጁ፡-

ፌስቡክ፡ https://www.facebook.com/EEUOfficial/
ቲዊተር፡ https://twitter.com/EEUEthiopia
ቴሌግራም፡ t.me/eeuethiopia
ዩቱዩብ: https://www.youtube.com/c/EthiopianElectricUtility
ድረ-ገፅ፡ http://www.eeu.gov.et/