Get Mystery Box with random crypto!

መረጃ ዳግም በተቀሰቀሰ ጦርነት ሕወሓት ሦስት የቆቦ ወረዳ ቀበሌዎችን መቆጣጠሩ ተነገረ በኢት | ንስር ዜና Eagle News Official

መረጃ

ዳግም በተቀሰቀሰ ጦርነት ሕወሓት ሦስት የቆቦ ወረዳ ቀበሌዎችን መቆጣጠሩ ተነገረ

በኢትዮጵያ መንግሥትና በሕወሓት መካከል ዳግም በተቀሰቀሰ ጦርነት ሕወሓት ሦስት የቆቦ ወረዳ ቀበሌዎችን መቆጣጠሩን የአካባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።

በሰሜን ወሎ ዞን ቆቦ ወረዳ የሚገኙ ስሚዛ ጊዮርጊስ፣ መቀነት ጋሪያ፣ ጃን አሞራ የተባሉት ቀበሌዎችን ሕወሓት መቆጣጠሩን የአካባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትና በአካባቢው ያሉ ሚሊሻዎች ታጣቂ ቡድኑ የሚሰነዝረውን ጥቃት ለመመከት ቢሞክሩም ይህ ዘገባ እስከተዘጋጀበት ጊዜ ድረስ ለጥቃት ምቹ የሆኑ ስትራቴጅክ ቦታዎች በሕወሓት ቁጥጥር ስር ናቸው ተብሏል።

ከዚህም በተጨማሪ በግዳን ወረዳ ሙጃና ላስታ አካባቢ አልፎ አልፎ የሕውሓት ቡድን ሰርጎ በመግባቱ ቦታው አፋጣኝና ልዩ ትኩረት እንደሚያሻው ነዋሪዎቹ ጥቆማ ሰጥተዋል። በደጋማው አካባቢ የሚገኙ ንጹሐን ዜጎችን ታጣቂ ቡድኑ ሚሊሻ ናችሁ በማለት እየገደለ ነው የተባለ ሲሆን፤ እስከ አሁን ቁጥራቸው በግልጽ ያልታወቁ ነገር ግን ከ10 በላይ እንደሚሆኑ የሚገመት ሰዎች መገደላቸውንም ነዋሪዎች ተናግረዋል።

ይህ እስከ አሁን የተረጋገጠ ነው እንጂ የሟቾች ቁጥር ከዚህ ሊልቅ እንደሚችልም ተመላክቷል። ከሰዎች መሞት በዘለለም የሚሊሻ ቤተሰብ ናችሁ በሚል ሰበብ ከዚህ ቀደም በነበረው ጥቃት የተረፈው የበርካታ ነዋሪዎች ንብረት እየተዘረፈ መሆኑን ነው አዲስ ማለዳ ከቦታው የሰማችው።

እስከ አሁን ከደረሰብን ግፍ በትክክል አላገገምንም ያሉት ነዋሪዎቹ፤ ታጣቂ ቡድኑ በሚያደርሰው ጥቃትና የማስፋፋት ድርጊት ስጋት እንዳደረባቸው ገልጸው፤ ከዚህ የከፋ ጉዳት ከመድረሱ በፊት የወገን ኃይል እንዲደርስላቸው አሳስበዋል።

(አዲስ ማለዳ)