2022-04-15 22:33:11
ነዋሪዎችን ያማረሩት ጫኝ እና አውራጆች ፦
ከቲክቫህ ቤተሰብ አባል ፦
" በአዲስ አበባ ከተማ ላይ በሁሉም ሰፈር ማለት ይቻላል በህገወጥ ጫኝና አውራጆች በሚጠየቅ የተጋነነ ክፍያ ምክንያት ዕቃ መኪና ላይ መጫንም ሆነ ማውረድ አዳጋች ሆኗል፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ እነዚህ ህገ ወጦች ላይ እርምጃ በመውሰድ ህብረተሰቡን ሊታደግ ይገባል።
ሰው ተሰቃይቷል ፤ ህዝቡ ተበሳጭቷል ፤ ጉረቤትህ እና ልጆችህ እንኳ ተባብረው ሊያራግፉልህ እድል አይሰጡም።
እነዚህ ወጣቶች ሌላው በመቶ ብር ሚያራግፈውን እነሱ ቢያንስ እስከ 3 ሺ ብር ይጠይቃሉ። "
ከሰሞኑን ከዚህ ነዋሪዎችን እያማረረ ካለው ህገወጥ ድርጊት ጋር በተያያዘ የአዲስ አበባ ፖሊስ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ለሸገር FM 102.1 ሬድዮ ጣቢያ በሰጠው ቃል አሳውቋል።
በአ/አ ፖሊስ ኮሚሽን የሚዲያ ዘርፍ ኃላፊ ምክትል ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ ፥
" ብዙ ችግር ነው ያለው። ለምሳሌ ፦
ቁሳቁሱን እኛ ብቻ ነን የምናወርደው ፤ የምንጭነው ብለው እራሳቸው ይወስናሉ በሰው ንብረት።
ተመጣጣኝ ክፍያ አይጠይቁም።
እርስ በእርስም የሚጣሉበት ሁኔታ አለ፤ በዚህም ንብረት ይወድማል አካል ጉዳት ይደርሳል። ምንም በማያገባው እዛ ባለው ግለሰብ ንብረት ላይ ጭምር ጉዳት ይደርሳል።
ግለሰቦችን ማጨነቅ አለ እኛ ካላወረድነው እናወድመዋልን የሚሉም አሉ።
ይሄ እጅግ በጣም ከባድ ነገር ነው። ስለዚህ ይሄን ስራ የሚሰሩ ሰዎች ተለይተው ህብረተሰቡ ለፖሊስ መረጃ በመስጠት አደብ እንዲገዙ መደረግ መቻል አለበት ካለበለዚያ ከባድ ስጋት ነው የሚሆኑት። " ብለዋል።
ፖሊስም የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት በህገወጥ ጫኝ እና አውራጆች ላይ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ምክትል ኮማንደር ማርቆስ አሳውቀዋል።
ም/ኮማንደር ማርቆስ ፦
" በለሚኩራ ክ/ከተማ በ6 ወር በ21 መዝገቦች 80 ተከሳሾች ይዘን ምርመራ እያጣራን ነው። በተመሳሳይ በ12 መዝገቦች 45 ተጠርጣሪዎች ማረሚያ ቤት ወርደው ጉዳያቸውን በህግ እንዲከታተሉ እየተደረገ ነው።
በቦሌ ክ/ከተማ በ10 መዝገቦች 63 ተከሳሾች ላይ ክስ ተመስርቷል። 62ቱ ተይዘዋል። እነዚህም ምርመራ እየተጣራባቸው ነው።
ንፋስስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ ሰፈራ የሚባል አካባቢ ባለፈው ወር የተሰራ ስራ በቀን 21/7/2014 ዓ/ም በአንድ መዝገብ 10 ተከሳሾች ይዘን ምርመራ እያጣራን ነው።
በለቡ ፖሊስ ጣቢያ ፤ ሆፕ ዩኒቨርሲቲ የሚባል አለ እዛ አፓርታማ ቤቶች አሉ እዛ የሚገቡ ሰዎች ላይ ችግር ሲፈጥሩ የነበሩ በአንድ መዝገብ 13 ተጠርጣሪዎች ተይዘው በ4ቱ ላክ ሁለት ሁለት ወር እንዲወሰንባቸው ተደርጓል " ሲሉ አስረድተዋል።
" አንዳንድ ስራቸውን በአግባቡ የሚሰሩ ጫኝና አራጆች አሉ ፤ በቅርቡም ጥይቶች ተጭነው እስከማጋለጥ የደረሱ መኖራቸውን ተመልክተናል " ያሉት ምክትል ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ ያልተገባ ስራ የሚሰሩትን ፤ ወደ ህግ ከማቅረብ ይልቅ #ተስማሙ የሚሉ የፖሊስ አባላትን ህብረተሰቡ ሲመለከት በ991 ነፃ የስልክ መስመር እና በ 0111110111 በመደወል ጥቆማ እንዲሰጥ ከሸገር ኤፍ ኤም ሬድዮ ጋር በነበራቸው ቆይታ ወቅት ጥሪ አቅርበዋል።
3.9K viewsTewodros Eshetu, 19:33