Get Mystery Box with random crypto!

ቅትለተ መነኮሳት ከዝቋላ ወደ ደቡብ አፍሪቃ አባ ተክለ ሃይማኖት (አባ ተክላ) ደቡብ አፍሪቃ ገጠ | የዲ/ን ሄኖክ ኃይሌ ትምህርቶች

ቅትለተ መነኮሳት ከዝቋላ ወደ ደቡብ አፍሪቃ

አባ ተክለ ሃይማኖት (አባ ተክላ) ደቡብ አፍሪቃ ገጠር ውስጥ የሚያገለግሉ መነኩሴ ነበሩ:: ወላጆቻቸው ለኢትዮጵያዊው ጻድቅ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ምልጃቸውን በመማጸን ተስለው ስለወለዱአቸው ስማቸውን በጻድቁ ስም ሰይመዋቸዋል:: ከባለጸጋ ቤተሰብ የተወለዱትና የሚተዳደሩበት የራሳቸው መርከብ የነበራቸው እኚህ ወጣት የእንጦንስ የመቃርስን መንገድ ተከትለው ሀብታቸውን ሸጠው ለድኆች ሠጥተው የቀረውን ለገዳም አውርሰው መነኮሱ:: ከዓመታት በፊት በገዳማቸው ተገኝቼ በረከት በተቀበልሁበት ወቅት እንዴት እንደመነኮሱ ፣ ለአቡነ ተክለ ሃይማኖት ያላቸውን ፍቅርና አንዳንድ ነገሮችን አጫውተውኝ ነበር:: ለእኔም ያሳዩት ስስትና ፍቅር ከሕሊናዬ የማይጠፋ ነው:: ዛሬ በግፍ ሰማዕትነትን እንደተቀበሉ ቢቢሲ ዘግቦ አየሁ:: ሰይጣን የእውነተኛይቱን ቤተ ክርስቲያን አድራሻ መቼም አይሳሳትም::

በግብፃዊው ጻድቅ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ስም በተሰየመ ገዳም የመነኮሱ ኢትዮጵያውያን ሰማዕታት በሆኑ በሳምንቱ በኢትዮጵያዊው ጻድቅ ተክለ ሃይማኖት ስም የተሰየሙ መነኩሴ ከወንድሞቻቸው ጋር ሰማዕትነት ተቀበሉ:: ሰይጣን ከሃይማኖታችን እንጂ ከዘራችን ጠብ የለውም::

ሰአሉ ለነ አስተምሕሩ ለነ
እስመ በጸሎተ ጻድቅ ትድኅን ሀገር

“በዚያን ጊዜ ለመከራ አሳልፈው ይሰጡአችኋል ይገድሉአችሁማል፥ ስለ ስሜም በአሕዛብ ሁሉ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ" ማቴ. 24:9

https://www.facebook.com/share/U25yhRDtJaBojkjB/?mibextid=WC7FNe