Get Mystery Box with random crypto!

በከበረች ጸሎቱ ይቅር ይበለንና ራሱን በትሕትና 'ከጌቶች ልጆች የሚወድቀውን ፍርፋሪ የሚለምን ውሻ' | የዲ/ን ሄኖክ ኃይሌ ትምህርቶች

በከበረች ጸሎቱ ይቅር ይበለንና ራሱን በትሕትና "ከጌቶች ልጆች የሚወድቀውን ፍርፋሪ የሚለምን ውሻ" ብሎ የሚጠራው ሶርያዊው ኮከብ ቅዱስ ኤፍሬም በየድርሰቶቹ መካከል እንዲህ እንዲህ አለ:-

"ጌታችን ከሣምራዊትዋ ሴት ጋር በተነጋገረ ጊዜ በንግግራቸው መጀመሪያ ማንነቱን አልገለጠላትም። መጀመሪያ ያየችው ውኃ የጠማውን ሰው ነበር ፣ ከዚያ አይሁዳዊ ፣ ከዚያ መምህር (ረቢ) ፣ ቀጥሎ ነቢይ ከሁሉም መጨረሻ መሲህ መሆኑን አየች።
ውኃ የተጠማውን ሰው በንግግር ልትረታ ስትሞክር በአይሁዳዊ ላይ ያላትን ጥላቻ አሳየች። ከመምህሩ ጋርም ተከራከረች ፣ ከነቢዩ እግር ስር ተንበረከከች ፣ መሲሁንም ወደደችው"
ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ (ስለ ሣምራዊቷ ሴት ዮሐ 4:1)

★ ★ ★

"ጌታ ሆይ ለእኛ ፊት ክብርን የሠጠ እንደ አንተ ያለ ማን አለ?
የዕውሩን ዓይን ባበራህለት ጊዜ ላድነው ነህ ብለህ በፊቱ ላይ አልተፋህበትም።
ነገር ግን አርኣያችንን አክብረህ በመሬት ላይ እንትፍ ብለው ፈወስከው።
ጌታዬ ሆይ በእኔ ላይ ግን በፊቴ ላይ እንትፍ በልብኝ ፣ በፈቃዴ ያጠፋሁትን ዓይኔን በፈቃድህ አብራልኝ"

ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ
(ዕውር ሆኖ ስለተወለደው ዮሐ 9:30)

★ ★ ★
"ጌታ ሆይ ዕውሩን ሂድ ብለህ ወደላክህበት ወደ ሰሊሆም መጠመቂያ አሁን ልንሔድ አንችልም። ነገር ግን ሕይወትንና ብርሃንን የተሞላው የከበረ ደምህ ያለበት ጽዋ በእኛ ዘንድ አለ። ከእርሱ በተቀበልን ቁጥር እንነጻለን" ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ

★ ★ ★

"ጌታዬ ሆይ በሔድኩበት ውጣውረድ የተሞላ መንገድ እምነቴ ደከመ ፣ መንገዱ የሚወስደኝም በግራ ወደሚቆሙት ፣ በደጅ ቆመው ክፈትልን ሲሉህ "አላውቃችሁም" ከምትላቸው ወገን ልሆን ነው።
ጌታዬ ሆይ እኔ አውቅሃለሁ ፣ አንተ ግን አላውቅህም ትለኝ ይሆን? አቤቱ በአንተ ለማምን ለእኔ ለኃጢአተኛው ራራልኝ። ብበድልህም እንኳን አሁንም በርህን እያንኳኳሁ ነው። እየተጎተትኩም ቢሆን አሁንም የምጓዘው ወደ አንተ ለመምጣት ነው"

ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ (ማቴ 7:7)
★ ★ ★

"ጌታ ሆይ እነዚህን በዕድሜ ሕፃናት የሆኑ የመንፈስ ልጆቼን ይቅር በላቸው። ሕፃን የነበርከው ሆይ የሕፃንነትህን ጊዜ አስብ። ልጅነታቸው ያንተን ልጅነት እንዲመስል አድርግላቸውና በቸርነትህ አድናቸው"
ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ከተለያዩ መዝሙራቱ (Hymns) በተርጓሚው ተለቃቅሞ የተሰበሰበ
ኅዳር 26 2011 ዓ ም
ክርስቲያን ሳንድ
Deacon Henok Haile