Get Mystery Box with random crypto!

+ ማርያማዊ ብሶት + 'ልጄ ሆይ ለምን እንዲህ አደረግህብን?' ድንግል ማርያም በመጽሐፍ ቅዱስ | የዲ/ን ሄኖክ ኃይሌ ትምህርቶች

+ ማርያማዊ ብሶት +

"ልጄ ሆይ ለምን እንዲህ አደረግህብን?"

ድንግል ማርያም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጻፈ የተናገረችው የብሶት ንግግር ይኼ ብቻ ነው:: "ልጄ ሆይ ለምን እንዲህ አደረግህብን?"

ድንግሊቱ እንዲህ ያለችው ምን ቢደርስባት ነው?

ጌዴዎን እስራኤል መከራ ሲጸናባቸው "ጌታዬ ሆይ፥ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ይህ ነገር ሁሉ ለምን ደረሰብን?" ብሎ ነበር:: መሳ. 6:13

ኢያሱም በጠላት እጅ በወደቁ ጊዜ :- ዋይ! ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ በአሞራውያን እጅ አሳልፈህ ትሰጠን ታጠፋንም ዘንድ ይህን ሕዝብ ዮርዳኖስን ለምን አሻገርኸው? ብሎ በብሶት አልቅሶ ነበር:: ኢያሱ 7:7

ሙሴም የሕዝቡ አመፅ ሲያስጨንቀው ሙሴም እግዚአብሔርን አለው፦ ለምን በባሪያህ ላይ ክፉ አደረግህ? ለምንስ የዚህን ሕዝብ ሁሉ ሸክም በእኔ ላይ አደረግህ? ብሎ ተማርሮ ነበር:: ዘኍ. 11:11

ድንግል ማርያም "ልጄ ሆይ ለምን እንዲህ አደረግህብን?" ብላ የብሶት ቃል የተናገረችው ግን መከራ ሲደርስባት አልነበረም::

ወደ ግብፅ ስደት እንድትወጣ ሲነገራት "ልጄ ሆይ ለምን እንዲህ አደረግህብን?" አላለችም:: ግርፋቱንና ሕማሙን ስታይም ኀዘንዋን ዋጥ አድርጋ ቆመች እንጂ "ልጄ ሆይ ለምን እንዲህ አደረግህብን?" አላለችም::

ድንግል ማርያም "ልጄ ሆይ ለምን እንዲህ አደረግህብን?" ያለችው ልጅዋ ለሦስት ቀናት ከዓይንዋ በራቀበት ወቅት ነበረ:: "እናቱም፦ ልጄ ሆይ፥ ለምን እንዲህ አደረግህብን? እነሆ፥ አባትህና እኔ እየተጨነቅን ስንፈልግህ ነበርን፡ አለችው" ሉቃ. 2:48

ድንግሊቱ ለምን እንዲህ አደረግህብኝ ያለችው ስለ ሌላው መከራዋ ጊዜ ሳይሆን ክርስቶስ ከእርስዋ ዘንድ ስላልነበረባቸው ቀናት ነበር:: እንደርስዋ መንፈሳዊ ስትሆን "ጌታ ሆይ ለምን አስጨነቅኸኝ?" የምትለው እርሱ ከአንተ የራቀ መሆኑ ሲሰማህ ብቻ ነው:: "አምላኬ አምላኬ ለምን ተውኸኝ? እኔን ከማዳንና ከጩኸቴ ቃል ሩቅ ነህ" "አቤቱ፥ ለምን ርቀህ ቆምህ?" እያልክ የምትጮኸው እግዚአብሔር ከአንተ የራቀ ሲመስልህና የተቀደሰው ማርያማዊ ብሶት ሲሰማህ ነው:: መዝ. 21:1፤10:1

እርሱ ከአንተ ጋር ከሆነ "በሞት ጥላ መካከል እንኩዋን ብትሔድ ክፉውን አትፈራም" ከአንተ የተለየ ሲመስልህ ግን "ጌታ ሆይ ምን አደረግህብኝ" ብለህ በማርያማዊ ብሶት ትጮኻለህ::

ከእርሱ ጋር ሆነህ መከራን መቀበል አይከብድህም:: መሰደድም አያስጨንቅህም:: እርሱ ከአንተ ዘንድ ከጠፋ ግን ብርሃንህ ምርኩዝህ ኃይልህ ጉልበትህ ሁሉ ከአንተ ዘንድ የሉምና ልትጸና አትችልም::

ዝምተኛዋን ድንግል ማርያም በብሶት ማናገር የቻለ አንዳች መከራ አልነበረም:: በበረሃ ከልጅዋ ጋር ከተንከራተተችበት ጊዜ ይልቅ ግን ያለ ልጅዋ ያሳለፈቻቸው ሦስት ቀናት "ልጄ ሆይ ለምን ይሄን አደረግህብኝ" ብላ እንድትጮህ አደረጓት::

ድንግል ሆይ ከአንቺ ዘንድ ለሦስት ቀን የተሰወረው ጌታ ከእኔ ሕይወት ከራቀ ዓመታት እንዳለፉ እያየሽ ይሆን? "ልጄ ሆይ ለምን እንዲህ አደረግህበት? ነፍሱ ተጨንቃ እየፈለገችህ አይደለምን?" የማትይው ስለምንድን ነው?

ለሌላው መከራዬ የምጮኸውን ያህል ከልጅሽ መለየቴ ተሰምቶኝ በማርያማዊ ብሶት እንዳልጮህ በኃጢአት ብርድ ተይዤ መንፈሳዊ ሙቀት በእኔ ዘንድ የለም:: የምበላው የምለብሰው ሲጎድል እንጂ አምላኬን ሳጣ የሚሰማኝ ሰው አይደለሁም:: እኔ ባልጠይቅሽ እንኳን እንደ ቃና ሙሽሮች ጉድለቴን አይተሽ የማትለምኚልኝ ለምንድን ነው? ልጅሽ ወደ ወይን እንዲለውጠው ከእኔ ሕይወት በላይ ውኃ ውኃ ያለ ነገር ከወዴት ሊመጣ? ከልቤስ በላይ የድንጋይ ጋን ከየት ይገኛል?

"ንዒ ማርያም ለዕውር ብርሃኑ
ወንዒ ድንግል ለጽሙዕ አንቅዕተ ወይኑ
ኦ ኦ ትኃድግኒኑ ኦ ኦ ትመንንኒኑ
ኀዘነ ልብየ እነግር ለመኑ"
"የዕውር ብርሃኑ ማርያም ሆይ ነይ
ለተጠማው ወይን የምታፈልቂለት ማርያም ሆይ ነይ
ወዮ ትተዪኝ ይሆንን? ወዮ ትንቂኝ ይሆንን?
የልቤን ኀዘን ለማን እነግራለሁ? (መልክአ ኤዶም)

ወተዘከርኒ ለኃጥእ ገብርኪ ተክለ ማርያም

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ነሐሴ 7 2015 ዓ.ም.