Get Mystery Box with random crypto!

ለነገሩ ለወላዋዩ ናቡከደነፆር ምን መልስ ይሠጣል፡፡ ታሪኩን ስናነብ እንደ ናቡከደነፆር ተገለባባጭ | የዲ/ን ሄኖክ ኃይሌ ትምህርቶች

ለነገሩ ለወላዋዩ ናቡከደነፆር ምን መልስ ይሠጣል፡፡ ታሪኩን ስናነብ እንደ ናቡከደነፆር ተገለባባጭ ሰው የለም፡፡ ትንቢተ ዳንኤል ምዕራፍ ሁለት ላይ ለፈጣሪ መሰከረ ፣ ምዕራፍ ሦስት ላይ ካደ ፣ ምዕራፍ ሦስት መጨረሻ ላይ አምኖ መሰከረ ፣ ምዕራፍ አራት መጀመሪያ ላይ ለፈጣሪ እንደ መዘመር ቃጣው በሕልሙ መልአክ እስከማየት ደርሶ ስለ ፈጣሪ ኃያልነት መሰከረ ፣ ምዕራፍ አራት መጨረሻ ላይ ግን ‹‹ይህች በጉልበቴ ብርታት ለግርማዬ ክብር የሠራኋት ታላቂቱ ባቢሎን አይደለችምን?›› ብሎ ተኮፍሶ እንደ እንስሳ ሣር እስኪግጥ ድረስ ተቀጥቷል፡፡ ስለዚህ ሦስቱ ወጣቶች ‹አምላካችሁ ማን ነው?› ሲላቸው መልስ ልንሠጥህ አያስፈልገንም ፤ አንተው ማን እንደሆነ ሣር ስትግጥ ታየዋለህ አሉት፡፡ እግዚአብሔር ማን ነው ያሉ እነፈርኦን የደረሰባቸው ባይገባህ አንተ ላይ ደርሶ ታየዋለህ ሲሉ ‹እንመልስልህ ዘንድ አስፈላጊያችን አይደለም› አሉት፡፡

ሦስቱ ወጣቶች አምላካችሁ ማን ነው የሚለውን ባይመልሱም ይህንን ግን አሉ ‹‹ንጉሥ ሆይ አምላካችን ከሚነድደው ከእቶኑ እሳት ያድነን ዘንድ ይችላል ከእጅህም ያድነናል› ንጉሥ ሆይ አምላካችን ኃይሉ ከእሳት በላይ ነው፡፡ ያለ እሳት ማንደድ ያለ ውኃ ማብረድ ይችላል፡፡ ከእሳቱ ያድነናል ፤ ‹ከእሳቱ ቢያድናችሁ ምን ዋጋ አለው ፤ ከእሳት ብታመልጡ ከእኔ አታመልጡም› ብለህ ታስብ እንደሆን ‹‹ከእጅህም ያድነናል›› አሉት፡፡

‹‹ነገር ግን ንጉሥ ሆይ እርሱ ባያድነንም አማልክትህን እንደማናመልክ እወቅ›› አሉት፡፡ ወጣቶቹ ‹ባያድነንም› ያሉት ተጠራጥረው አይደለም፡፡ ለጣዖት ከመስገድ ሞት ይሻለናል ፣ ለጣዖት በመስገድ የምንጎዳው ጉዳት በእሳት ተቃጥለን ከምንጎዳው አይብስም ፣ የዘላለም እሳት ከሚፈጀን የአንተ እሳት ቢፈጀን እንመርጣለን ለማለት ነበር፡፡ በዚያ ላይ ሦስቱ ወጣቶች ‹ያድነን ዘንድ ይችላል› አሉ እንጂ ‹እንድናለን› አላሉም፡፡ የፈጣሪያቸውን የማዳን ኃይል በእርግጠኝነት ተናገሩ እንጂ ከዚህ እሳት እንደሚድኑ በእርግጠኝነት አልተናገሩም፡፡ ይህም ከትሕትናቸው የተነሣ ነበር፡፡ እግዚአብሔር መላእክቱን ስለ እኔ ያዝዝልኛል ያድነኛል ብሎ ወደ ሞት ራስን መሥጠት ጌታችን ለዲያቢሎስ እንዳለው ጌታ አምላክን መፈታተን ነው፡፡ ስለዚህ ሦስቱ ወጣቶች ‹ባያድነን እንኳን› ሲሉ ምግባራችን ከልክሎት ባያድነን እንኳን ያልዳነው በኃጢአታችን ነው እንጂ አምላካችን ማዳን ተስኖት እንዳይመስልህ አሉት፡፡

እነዚህ ወጣቶች ምንኛ ያስደንቃሉ ፤ ስለ ትንሣኤ ሙታን ባልተሰበከበት በዚያ ዘመን ፣ ምንም እንኳን ሥቃይ የማይነካቸው ቢሆንም እንኳን ጻድቃንም ቢሆኑ ወደ ሲኦል በሚወርዱበት በዚያ ዘመን ተስፋ ሳይኖር ተስፋ አድርገው እንደ ሐዲስ ኪዳን ሰው ወደ ሞት የሔዱት እነዚህ ወጣቶች ምንኛ ክቡራን ናቸው፡፡ ለዚህም ነው ሰማዕቱ ዮስጦስ (Justine the martyr) ‹‹ከክርስቶስ በፊት የነበሩ ክርስቲያኖች›› (Christians before Christ) የሚላቸው፡፡

★ መርጦ የሚያነድ እሳት ★

ናቡከደነፆር በወጣቶቹ መልስ እጅግ ተበሳጨ ፤ የሚነድደውን እሳት ሰባት እጥፍ እንዲያደርጉት አዘዘ፡፡ ልፋ ሲለው ነው እንጂ እሳቱ ሰባት እጅም ቢሆን ፣ አንድ እጅም ቢሆን ለሦስቱ ወጣቶች መቃጠል ያው መቃጠል ነው፡፡ የባቢሎንን ማገዶ ከማባከን በቀር ሦስቱ ወጣቶች የሚሞቱት ሞትም ያው አንድ ሞት ነው፡፡ የተፈለገው ግን እንዲፈሩ ነበር፡፡ ሰይጣን አሠራሩ እንዲህ ነው ፤ እምነታችን ሲጨምር እሳቱ ሰባት እጥፍ ይጨምራል፡፡ ‹ያድነናል› የሚለው ምስክርነታችን ናቡከደነፆሮችን ያስቆጣል፡፡ በሥልጣናቸው የሚነድደውን እሳት መጨመር እንጂ የእኛን እምነት መቀነስ አይችሉም፡፡ ሦስቱን ወጣቶች ከሰናፊላቸው ፣ ከቀሚሳቸውና ከመጎናጸፊያቸው ከቀረው ልብሳቸውም ጋር እንዲታሠሩ ተደረገ፡፡ ያ ሁሉ ልብስ አብሮአቸው እንዲታሰር የተፈለገው ሥቃያቸውን የበለጠ ለማብዛት ፣ እግራቸው መታሰሩም ሳይንፈራገጡ እንዲቃጠሉ ለማድረግ ነበር፡፡ በዚህ አሰቃቂ ሁኔታ ሦስቱን ወጣቶች ወደ እሳት ጨመሯቸው፡፡ ከእሳቱ ኃይል የተነሣ ‹የጣሏቸውን ሰዎች የእሳቱ ወላፈን ገደላቸው›

ሦስቱን ወጣቶች እሳት ውስጥ ሲገቡ ከእስራቸው ተፈትተው ሲመላለሱ ታዩ ፤ ናቡከደነፆር ባላዋቂ አነጋገር ‹የአማልክት ልጅ› ያለውን ‹የእግዚአብሔር ልጆች› ተብለው ከሚጠሩት መላእክት አንዱ የሆነውን መልአኩን ልኮ የእሳቱን ኃይል አጠፋ፡፡ ‹የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ዙሪያ ይሠፍራል ያድናቸውማል› የተባለውም ተፈጸመ፡፡ ‹የአማልክት ልጅ› የተባለው የመልአኩ መውረድ የወልደ እግዚአብሔር የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ፣ የመምጣቱና የሰውን ልጅ ከሲኦል እሳት የማዳኑ ሥራ ምሳሌ ሆኖ ይኖራል፡፡

ሦስቱ ወጣቶች ልብስ አልብሰው የጨመሯቸው እንዲሰቃዩ ነበር ፤ ሆኖም ለሥቃይ የለበሱት ልብስ ለዝማሬ ሆናቸው፡፡ መቼም ዕርቃን ሆኖ ዝማሬ የለም፡፡ አልብሰው ባይከቷቸው ኖሮ ሲወጡ ዕርቃናቸውን በወጡ ነበር፡፡ የሚያስደንቀው እነዚህ ሦስት ዕፀ ጳጦሶች እንኳን ሊቃጠሉ ጭስ ጭስ እንኳን አይሉም ነበር፡፡
የባቢሎን እሳት አስደናቂ እሳት ነው፡፡ ከእሳቱ ውስጥ እያሉ እሳቱ ያቃጠለው የታሰሩበትን ገመድ ብቻ ነበር፡፡ ከዚያ ውጪ የጣሏቸውን ሰዎች ወላፈኑ ገደላቸው፡፡ ሰዎችን ወደ እሳት መገፍተር ቀላል ነው፤ እሳቱ ግን ገፍታሪዎቹን ሊያቃጥል ይችላል፡፡ ‹‹እሳት በላዒ ለአማፅያን ለእለ ይክህዱ ስሞ ፤ ወእሳት ማኅየዊ ለርቱዓነ ልብ ለእለ ይገብሩ ፈቃዶ›› (ስሙን ለሚክዱ ለአመጸኞች የሚባላ እሳት ነው ፤ፈቃዱን ለሚሠሩ ልባቸው ለቀና የሚያድን እሳት ነው) የሚለው የአባ ሕርያቆስ ቅዳሴ በብሉይ ኪዳን ቢሆን ለባቢሎን እሳት ይሠራ ነበር፡፡

ሦስቱ ወጣቶች እሳት ውስጥ ገብተው የመውጣታቸው ታሪክ በጥላቻና በዘረኝነት እሳት እየነደድን ባለንበት በዚህ ዘመን ሆነን ስንመለከተው መልእክቱ ብዙ ነው፡፡ በሚነድደው እሳት ላይ የእያንዳንዳችን ድርሻ ምንድር ነው? አንዳንድ ሰው ‹ይለይለት ካልደፈረሰ አይጠራም› ይላል፡፡ በስድብ በጥላቻ በነቀፋ ከሩቅም ከቅርብም ሆኖ የሚያባብስ ሰው እንግዲህ እሳቱን ሰባት እጥፍ ከሚጨምሩት የናቡከደነፆር አሽከሮች አይለይም፡፡ በዚያ ላይ ይለይለት ብለህ የምትጨምረው እሳት ወላፈኑ አንተኑ ማቃጠሉ አይቀርም፡፡ ያለነውም የምንኖረውም እሳቱ ውስጥ ሆነው ‹‹የምናመልከው አምላክ ሊያድነን ይችላል›› ብለው በሚጸልዩ ሰዎች ነው፡፡ ጸሎት መፍትሔ ነው ሲባል በሚያስቀን በናቡከደነፆሮች ሳይሆን ዳዊቱን በማያስታጉሉ አናንያ አዛርያና ሚሳኤሎች ነው፡፡

እሳት ውስጥ ገብተው የወጡት እነዚህ አርበኞች ከጸሎቱ ባሻገር አንድ ልብ ነበሩ፡፡ በሙሉ ትንቢተ ዳንኤል ላይ ‹አናንያ እንዲህ አለ ፤ አዛርያም እንዲህ አለ› የሚል አልተጻፈም፡፡ ሦስት ሲሆኑ እንደ አንድ ሰው ሲናገሩ ሲሰሙ ፣ አብረው ሲጾሙ ፣ አብረው ሲሾሙ ፣ አብረው ሲታሰሩ ፣ አብረው ከእሳት ሲገቡ አብረው ሲወጡ ፣ አብረው ሲዘምሩ ነው ያየናቸው፡፡ አንድ ልብ ሳይሆኑ ከእሳት መውጣት አይቻልም፡፡ አናንያና አዛርያ ተፋቅረው ሚሳኤልን ቢጠሉት ኖሮ በሃሳብ ባይስማሙ ኖሮ ተቃጥለው ይቀሩ ነበር፡፡ ‹‹መልአኩን የላከ በእርሱ የታመኑትን ባሪያዎቹን ያዳነ የአናንያ የአዛርያ የሚሳኤል አምላክ ይባረክ›› (ዳን. 3፡28)

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ታኅሣሥ 19/2011 ዓ.ም.
ኦስሎ ኖርዌይ