Get Mystery Box with random crypto!

+ የዝምታ ጩኸት + እስራኤል ጭንቅ ላይ ናቸው:: ከባርነት ተላቅቀው ከግብፅ ከወጡና ጉዞ ከጀመ | የዲ/ን ሄኖክ ኃይሌ ትምህርቶች

+ የዝምታ ጩኸት +

እስራኤል ጭንቅ ላይ ናቸው:: ከባርነት ተላቅቀው ከግብፅ ከወጡና ጉዞ ከጀመሩ በኁዋላ ፈርኦን የለቀቀው ሕዝብ ጉልበት ቆጭቶት በቁጣ ነድዶ ሠራዊቱን አስከትቶ በፈጣን ሠረገላ እየጋለበ መጣባቸው:: ከፊታቸው ደግሞ የሚያስፈራ ባሕር ተደቅኖአል::

ሕዝቡ የፈረደበት ሙሴ ላይ ጮኹበት:: መጽሐፈ መቃብያን "ያንን ሁሉ ሕዝብ ሲጠብቅ ያልተበሳጨ ሙሴን አስበው" እንደሚል እንደ ሙሴ ትሑትና ታጋሽ መሪ ታይቶ አይታወቅም:: ልክ በዚያች ዛፍ ላይ እሳት ሲነድባት እንዳልተቃጠለች እስራኤላውያንም ሙሴ ላይ ለዓመታት ቢነዱም አላቃጠሉትም::

"በግብፅ መቃብር ጠፍቶ ልታስፈጀን ነው?" "ከሞት ባርነት በስንት ጣዕሙ?"
እስራኤል በኤርትራ ባሕር ዳርቻ ሙሴን በቁጣ እየጮኹ አስጨነቁት::

መሪነት ከባድ ነው:: ያንን ሁሉ ድንቅ ነገር አድርጎ እግዚአብሔር ነፃ ሲያወጣቸው ሙሴ ለእነርሱ ቤዛ ሆኖ ተሹሞ ብዙ ዋጋ ከፍሎአል:: ውለታውን ረስተው አፋጠጡት::

"ሙሴም ለሕዝቡ፦ አትፍሩ፥ ዛሬ የምታዩአቸውን ግብፃውያንን ለዘላለም አታዩአቸውምና ቁሙ፥ ዛሬ ለእናንተ የሚያደርጋትን የእግዚአብሔርን ማዳን እዩ። እግዚአብሔር ስለ እናንተ ይዋጋል፥ እናንተም ዝም ትላላችሁ፡ አላቸው"

ሙሴ ሕዝቡን ከጩኸታቸው ሲያረጋጋ ሳለ የእግዚአብሔር ድምፅ ወደ ሙሴ መጣ
"ሙሴ ሆይ ለምን ትጮኽብኛለህ?" አለው::

ልብ አድርጉ የጮኸው ሕዝቡ ነው ሙሴ አረጋጋ እንጂ ቃል አልተናገረም::

ሆኖም ሙሴ አፉ ዝም ቢል ልቡ ይጮኽ ነበር:: ከእስራኤል ጩኸት ይልቅ የሙሴ ዝምታ እግዚአብሔር ጆሮ ደረሰ:: እግዚአብሔር ኤልያስ እንዳላገጠባቸው የአሕዛብ አማልክት በጩኸት ብዛት የሚሰማ አምላክ አይደለም:: በትዕቢትና አመፅ ከሞላበት ጩኸት ይልቅ በተሰበረ ልብ የሚቀርብ ዝምታ እግዚአብሔር ጋር ይጮኻል::

የእስራኤል ጩኸት ፍርሃት ይነዛል:: ልናልቅ ነው የሚል ሽብር ይፈጥራል:: የሙሴ ዝምታ ግን ባሕር ይከፍላል::

ጌታ ሆይ ጩኸታችን አልሆነልንም:: ዝምታችንን ሰምተህ ሀገራችንን ከከበባት ጥፋት ታደግልን::
የእኛ መጨቃጨቅና ጠብ ባሕር አይከፍልም::
የእኛ ጩኸት ከመነካከስ በቀር አያሻግርም::
በአርምሞ የሚለምኑህን በእኛ ፊት ዝም አሉ የምንላቸው በአንተ ፊት ግን የሚጮኹትን ሰምተህ ታደገን::

የኤርትራ ባሕር በዝምታ ተከፈለ:: እስከ ራማ የተሰማው ራሔል ስለ ልጆችዋ ያለቀሰችው ዕንባ ባሕር ከፈለ:: እመቤታችን ሆይ ስለ እኛ ስለልጆችሽ እባክሽን አልቅሺ:: የራሔል ዕንባ ራማ ከደረሰ የአንቺ ዕንባ የት ሊደርስ ነው? በየበረሃ እየወደቀ ስላለው ልጅሽ ስለሞተለት ወንድም እባክሽን ለምኚ::

በሙሴ በትር ባሕሩ ተከፈለ:: የኤርትራ ባሕር (ቀይ ባሕር [በግሪኩ erythos ማለት ቀይ ነው]) እጅግ ባለ ታሪክ ባሕር ነው:: ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ደረቅ ሆኖ ፀሐይ ያየውና ግማሽ ሚልየን የሚሆን ሕዝብ በመካከሉ ተራምዶ ያለፈበት ይህ ባሕር እንንደ ግድግዳ የቆመ ብቸኛው የዓለማችን ባሕር ነው::

በዚህ ባሕር እስራኤል ሲሻገሩ ፈርኦን ከነሠራዊቱ ሰጠመ:: በእግር የሔዱት የተሻገሩትን ባሕር በሠረገላ የሔዱት አቃታቸው:: የኤርትራ ባሕር ለእስራኤል ትንሣኤ ሲሆን ለፈርኦን ግን መቃብር ሆነ:: ፈርኦን ደንግጦ መመለስ የነበረበት ባሕሩ ሲከፈል ሲያይ ነበር:: ፈርኦንን ያደቆነ ሰይጣን ግን ባሕር መካከል ሳያቀስስ አልለቀቀውም::
እግዚአብሔር ማን ነው? ብሎ ነበር በዚያ ባሕር ተዋወቀው:: እሱ ሲሰጥም እስራኤል በኩራት "እግዚአብሔር ማን ነው? " ለሚለው የፈርኦን ጥያቄ ከባሕር ማዶ ሆነው መልስ ሠጡ "እግዚአብሔር ተዋጊ ነው ስሙም እግዚአብሔር ነው" አሉ:: እስራኤል በኤርትራ ባሕር መሻገራቸው የጥምቀት ምሳሌ ሆኖ "በባሕርና ደመና ተጠመቁ" ተብሎላቸዋል:: ፈርኦን ግን እስራኤል በተጠመቁበት ጠበል ውስጥ ሰጠመ::

የኤርትራን ባሕር ሲሻገሩ ከሙሴ ሌላ እስራኤልን ሲመራ የነበረ ጠባቂ ነበረ:: እርሱም የእስራኤል ጠባቂ (advocate of Israel) በመባል የሚታወቀው ቅዱስ ሚካኤል ነበር::

"በእስራኤልም ሠራዊት ፊት ይሄድ የነበረው የእግዚአብሔር መልአክ ፈቀቅ ብሎ በኋላቸው ሄደ፤ የደመናውም ዓምድ ከፊታቸው ፈቀቅ ብሎ በኋላቸው ቆመ" ዘጸ 14:19 እንዲል ቅዱስ ሚካኤል እስራኤልን ቀን በደመና ሌሊት በብርሃን ዐምድ እየተመሰለ በመንገድ መራቸው::

ኢትዮጵያውያን ያለነው ከባሕሩ ዳርቻ ላይ ነው:: ሁሉም መሻገር ይፈልጋል:: ከእኛ መካከል እንደ ፈርኦን ሰጥሞ የሚቀር ይኖራል:: እንደ እስራኤል የሚሻገር ይኖራል: : ቅዱስ ሚካኤል ሆይ ለእኛም ድረስልን:: ይህንን ክፉ ዘመን በክንፎችህ አሻግረን::

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ኅዳር 12 2013 ዓ ም
ድሬደዋ ኢትዮጵያ

ለተጨነቀች ነፍስ ዕረፍት የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ለሁሉ ይዳረስ ዘንድ :: እኔም ለእናንተ ከሰበክሁ በኁዋላ የተጣልሁ እንዳልሆን ስለ እኔ ጸልዩ!