Get Mystery Box with random crypto!

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሲቢኢ ኑር የባንክ አገልግሎት የኢፍጣር መርሐ-ግብር በአዲስ አበባ አከናወ | Commercial Bank of Ethiopia - Official

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሲቢኢ ኑር የባንክ አገልግሎት የኢፍጣር መርሐ-ግብር በአዲስ አበባ አከናወነ።
======================
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1445ኛውን የረመዷን ፆምን በማስመልከት ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች እና ለደንበኞቹ  መልካም ምኞት ለመግለጽ እና ያለውን አጋርነት  ለማሳየት ዛሬ መጋቢት 13 ቀን 2016 ዓ.ም ምሽት የኢፍጣር ሥነ-ሥርዓት በሸራተን አዲስ ሆቴል አከናውኗል፡፡

በመርሐ-ግብሩ ላይ ለተገኙ እንግዶች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት ያስተላለፉት የባንኩ የሲቢኢ ኑር አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ኑሪ ሁሴን የዘንድሮውን የኢፍጣር መርሀ ግብር ለየት የሚያደርገው ባንኩ ከውለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት የጀመረበትን 10ኛ ዓመት በድምቀት ባከበረ ፣ የሲቢኢ ኑር ተቀማጭ ገንዘብ 100 ቢሊዮን በተሻገረበት እንዲሁም የዘጠነኛው ዓለም አቀፍ የኢስላሚክ ሪቴይል ባንኪንግ ሽልማት ባገኘበት ማግስት መሆኑን ገልፀዋል።

በኢፍጣር መርሐ ግብሩ ላይ በመገኘት መልእክት ያስተላለፉት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሸሪዓ አማካሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶ/ር ሼህ ሙሀመድ ሀሚዲን ባንኩ የሸሪዓ መርሆዎችን የተከተለ አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆኑን ገልፀው፣ ሙስሊሙ ማህበረሰብ ከባንኩ ጋር በጋራ በመሆን  አገልግሎቱን ማሳደግ እንደሚጠበቅበት ተናግረዋል።
 
የኢትዮጵያ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ በበኩላቸው የኢፍጣር መርሀ ግብሩን በዘጉበት ንግግር የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሙስሊሙ ማህብረሰብ ትልቅ ባለውለታ መሆኑን በመግለፅ ምስጋና አቅርበዋል።

በመርሐ-ግብሩ ላይ የመንግስት የሦራ ኃላፊዎች፣ የሃይማኖቱ አባቶች፣የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሲቢኢ ኑር የሸሪዓ መማክርት ኮሚቴ አባላት፣ ደንበኞች እና የባንኩ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ156 ሙሉ በሙሉ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ብቻ በሚሰጡ ቅርንጫፎች እንዲሁም ከ1,940 በላይ በሚሆኑ ቅርንጫፎች ለአገልግሎቱ ብቻ በተለየ መስኮት የሲቢኢ ኑር ከወለድ ነፃ የባንክ  አገልግሎቶችን በመስጠት ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡

ባንካችን ቀሪው የረመዷን ወር በሰላም እንዲፈፀም  መልካም ምኞቱን ይገልፃል፡፡