Get Mystery Box with random crypto!

ቶሌ ቀበሌ በሸኔ ጥቃት ሊፈጸምብ ነው ሲሉ ስጋታቸውን ገለጹ! ባለፈው ዓመት ሰኔ በመቶዎች የሚቆጠ | ብሩህ ወቅታዊ ዜና

ቶሌ ቀበሌ በሸኔ ጥቃት ሊፈጸምብ ነው ሲሉ ስጋታቸውን ገለጹ!

ባለፈው ዓመት ሰኔ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በታጣቂዎች የተገደሉባት ቶሌ ቀበሌ ነዋሪዎች ዳግም ተመሳሳይ ጥቃት ሊፈፀምብን ይችላል በሚል ስጋት አካባቢያቸውን ለቀው መውጣታቸውን ገለጹ።

ባለፈው ዓመት ሰኔ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በታጣቂዎች የተገደሉባት ቶሌ ቀበሌ ነዋሪዎች ዳግም ተመሳሳይ ጥቃት ሊፈፀምብን ይችላል በሚል ስጋት አካባቢያቸውን ለቀው መውጣታቸውን ገለጹ።

ከአራት ወራት በፊት ምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ ውስጥ መንግሥት በሽብርተኛ ቡድንነት ሰይሞ ሸኔ በሚል የሚጠራው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት 400 የሚሆኑ ሰዎች መገደላቸውን የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ሂዩማን ራይትስ ዎች ገልጾ ነበር።

በአብዛኛው የአማራ ብሔር ተወላጆች የሆኑ ነዋሪዎችን ኢላማ አድርጎ በነበረው ጥቃት በርካታ ሴቶችና ህጻናት ሰለባ በሆኑበት በዚያ ጥቃት የተገደሉት ነዋሪዎች ቁጥር 338 መሆኑን የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ መግለጹ ይታወሳል። 
በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈው ይህ ጥቃት ከተፈጸመ ከጥቂት ወራት በኋላ የአማር ብሔር ተወላጅ የሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች ተመሳሳይ ጥቃት ሊፈጸም ይችላል በሚል የደኅንነት ስጋት ከቶሌ ቀበሌ ተፈናቅለው መውጣታቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ለደኅንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የቀበሌው ነዋሪዎች በአካባቢው የነበረው የፌደራል መንግሥቱ የፀጥታ ኃይሎች እንዲወጡ እንደነገሯቸውና አርብ ሌሊት ዘጠኝ ሰዓት ተነስተው ለሰዓታት በመጓዝ በምሥራቅ ወለጋ በሚገኘው አርጆ ጉደቱ ወደተባለ አካባቢ መሸሻቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የሁለት ልጆች እናት የሆነች ሴት ከዚህ ቀደም ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ በስፍራው የፌደራል ፖሊስ ተሰማርቶ እንደነበረ ገልጻ፣ ባለፈው ዓርብ ጥቅምት 25/2015 ዓ.ም. ከቦታው እንደሚለቁ ነግረውን “ሕይወታችሁን ለማትረፍ ውጡ እንሸኛችሁ” አሉን ስትል ትናገራለች።

ሌላኛው የቶሌ ቀበሌ ነዋሪ የሆነው እና የአራት ልጆች አባት የሆነው ግለሰብ እንደገለጸው፣ በስፍራው ሰፍረው የነበሩት የፌደራል ፖሊስ አባላት ከእኩለ ለሊት በኋላ 9 ሰዓት ላይ መኖሪያ ቤታቸው ድረስ በመምጣት አካባቢውን ጥለው እንዲወጡ እንደነገሯቸው ለቢቢሲ ተናግሯል።

“ከእንቅልፍ ቀስቅሰው ተነሱ አሉን። የምናውቀው ነገር የለም በእግር ተጉዘን አምስት ሰዓት አርጆ ደረሰን” የሚለው ነዋሪው ከቀያቸው በድንገት በመውጣታቸው ምንም ነገር ሳይዙ መውጣታቸውን ያስረዳሉ።

ከስድስት የቤተሰብ አባላቷ ጋር ከቶሌ ቀበሌ የወጣች ሌላ እናት ደግሞ “ከዚህ በፊት ብዙዎች እዚያው ከፊታችን ታርደውም፣ ተቃጥለውም ሲገደሉ ስላየን ሕይወታችንን ለማዳን ስንል ወጣን” ስትል ትናገራለች።

ከዚህ በፊት በቶሌ ቀበሌ በንጹሃን ዜጎች ላይ ግድያ የተፈጸመው የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ጥቃቱን ለመከላከል በቂ ጥበቃ ባለማደረጋቸው ነው ተብሎ ነበር።

     ( ቢቢሲ አማርኛ )