Get Mystery Box with random crypto!

በቅድሚያ ጀግናው ልጃችን ቴዲ አፍሮ፦ እንኳን ለኢትዮጵያ ልጇ፥ ለልጆቿም ወንድሞቿ ሆነህ ተወለድክል | Amleset Muchie

በቅድሚያ ጀግናው ልጃችን ቴዲ አፍሮ፦ እንኳን ለኢትዮጵያ ልጇ፥ ለልጆቿም ወንድሞቿ ሆነህ ተወለድክልን። ብዙዎች በዚህ ዓለም ላይ "ከከባድ ነገሮች ውስጥ አንዱ ከባድ ነገር የሚወዱትን ሰው በሚመጥኑ ቃላቶች ለመግለጽ መሞከር ነው" ሲሉ አውቃለሁ። በዚህ ጉዳይ በተወሰነ መልኩ ብስማማም ልቤ ግን አንደበት ከሚገልጸው በላይ ተግባር የሚገልጸው ፍቅር ይልቃል ብሎ ስለሚያምን ይኼን ሰው ለመግለጽ ቸገረኝ ብሎ ከማውራቱ ይልቅ እሱን በእውነተኛ የመውደድ ስሜት መውደዴ ብቻ በቂ ሆኖ ይሰማኛል። እንደ ቴዲ አፍሮ በጀግንነት እና በእርሱ ጽናት ልክ ባይሆንም ጥቂት ነገሮቹን በመውረስ ለአንዲትም ሰከንድ ቢሆን ሀሳቡን ሳልቋወም ከ20 አመታቶች በላይ ከርሱ ጋ ተጉዣለሁ። ይኼ እና ያልገለጽኳቸው እውነታዎች በተግባር የተገለጸውን ፍቅሬን በመጠኑም ቢሆን ይልጻሉ ብዬ አምናለሁ።

ሰውን ለመውደድ ሰው ከመሆን የላቀ ምክኒያት ባያስፈልግም የሰዎች አፍ ግን ስለምን ወደድከው ሲል ዕልፍ ጊዜ ጠይቆኛል። በመጀመሪያ ሰው በመሆኑ እንደ ሁሉ ሰው እንደወደድኩህ በኩራት ተናገርኩ። በመቀጠልም የእርሱን ስብዕናዎች እንዲ እያልኩ መጥቀስ ጀመርኩ። ቴዲ አፍሮን በጣም የወደድኩት ከሌሎቹ በተለየ መልኩ በሙዚቃዎቹ ስለ ፍቅር በጽኑ መንፈስ ስለሚያቀነቅን ነው። እኔ ደግሞ የፍቅርን ኃያልነት የማምን ሰው ነኝ። ፍቅር በእግዚአብሔር ከመወደድ እና እግዚአብሔርን ከመውደድ ይጀምራል። እግዚአብሔርን የሚወድ ሁሉ ሌሎችን ይወዳል። ይኼ የፍቅር ሉዓላዊ /ነጻ/ ህግ ነው።

ታዲያ ስለፍቅር ሌልች አላዜሙም እንዴ ብሉኝ ነጥቤ እሱ አይደለምና ሃሳቤን እንዲህ ስል እቀጥላሉ። ፍቅር ማለት መውደድ ብቻ አይደለም። መፍራት እና ማክበርም ጭምር ነው። በመፍራት የሆነ ማክበር እና አምልኮ ለእግዚአብሔር፥ በማክበር የሆነ መፍራት ደግሞ ለሰው ልጆች እና ለፍጥረት ሁሉ ይገባል። ይኼን መንፈስ የተጎናጸፈ ሰው ደግሞ ታላቁንም ታናሹንም ያከብራል፣ ይወዳል ይፈራልም። መፍራት በሃይለ ቃል ላላመናገር ነው። መፍራት ከላይም ከታችም በማሃከልም ለቆመው ለመታዘዝ መፍቀድን እንደ ሆነ ልብ ይሏል። ከዚህ አንጻር በኪነጥበቡ ዘርፍ እንዲህ ሆኖ ያገኘሁት ይኼንን ሰው ነው። ይኼንን ሰው መውደድ፣ ማክበር፣ መታዘዝ እንዲሁም እንደ ታላቅ ወንድም ማየት ፍጹም ጤናማ ከሆነ ልብ እና አዕምሮ የሚመነጭ ነው። በእግዚአብሔርም ዘንድ መውደድ ለሰው ልጆች ሁሉ የቀረበ የክርስቶስ አዋጅ ነውና ይኼን ሰው በመውደዴ ደስተኛ ነኝ እላለሁ በኩራት።

በመጨረሻም ለኢትዮጵያ አገራችን እና ለወገኖቻችን ላበረከተው አስተዋጽኦ ከፍ ያለ ምስጋናዬን ለማቅረብ እወዳለሁ። የኪነጥበብ ሙያው እንዲከበርና እንዲታፈር ጭምር የእርሱ በዚህ ደረጃ መግዘፍ ዋናውን ሚና ተጫውቷል ለዚህም ትልቅ ክብርን እሰጠዋለሁ። ቴዲ አፍሮ በሚወዱት፣ በሚጠሉት፣ በሚተቹት /በሚቀኑበት/ ባለሙያዎች ልብ ውስጥ ሳይቀር ትልቅነቱ ሊገዝፍ የቻለው እግዚአብሔርን ይዞ በመቆሙ ስለሆነ እግዚአብሔር እስከ ፍጻሜው ድረስ አብሮት ይሆን ዘንድ መልካም ምኞቴ ነው።

ትንሽ ልከትብ ፈልጌ ብዕሬን አነሳሁት ግን ትልቅ ሰው ሆነብኝ እና በትንሽ አንቀጽ ልቋጨው ተሳነኝ። አሁንም ብዙ ጠልቄ መውጫው እንዳይጠፋኝ የልቤን ሀሳብ ገትቼ ምኞቴን ገልጬ ልተው። በእውነተኛ መውደድ የምወድህ የክቡር ዶ/ር አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን /ቴዲ አፍሮ/ መልካም ልደት ይሁንልህ። የሚወድህ ልቤ የጸነሰውን ሀሳብ በሚያከብርህ ብዕሬ እንዲህ ከተብኩት።

✎ #ታታ_አፍሮ /ነፃ ብዕር/