Get Mystery Box with random crypto!

መንግሥት በቤተ ክርስቲያን ላይ የደቀነውን የህልውና አደጋ እና በንጹሃን ዜጎች ላይ እያደረሰ ያለው | አማራ ሚዲያ ማዕከል Amhara media center

መንግሥት በቤተ ክርስቲያን ላይ የደቀነውን የህልውና አደጋ እና በንጹሃን ዜጎች ላይ እያደረሰ ያለውን የከፋ በደልን የሚያወግዝ አለም አቀፍ የተቃውሞ ሰልፍ ሊጠራ ነው።

የአማራ ሚዲያ ማዕከል (አሚማ)
ግንቦት 16/2015 ዓ/ም
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ

በዋሽንግተን ዲሲና አካባቢው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህናትና ምዕመናን ኅብረት እንዳስታወቀው መንግሥት በቤተ ክርስቲያን ላይ የደቀነውን የህልውና አደጋ እና በንጹሃን ዜጎች ላይ እያደረሰ ያለውን የከፋ በደልን የሚያወግዝ አለም አቀፍ የተቃውሞ ሰልፍ ሊጠራ ነው።

በመንግሥት ጣልቃ ገብነት እና አቀናባሪነት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ውስጥ በጥር ወር የተከሰተው የሕገ ወጥ ሹመት ችግሩ ያልተቀረፈ ከመሆኑም ባለፈ መንግሥት ስልቱን በመቀያየር ያቀደውን ትልም ለማስፈጸም በትጋት እየሰራ ይገኛል ብሏል ህብረቱ በመግለጫው።

አሁንም መንግሥት በቀጥታ ከቅዱስ ሲኖዶስ አባላት መካከል ለራሱ አጀንዳ አስፈጻሚ ሊሆኑ የሚችሉ ሊቃነ ጳጳሳትን በመመልመል ዓላማውን ለማስፈጸም ቅዱስ ሲኖዶስን የመክፈል ሥራ እየሠራ መሆኑ የአደባባይ ምስጢር መሆኑን ጠቅሷል።

ለዚህም ዐቢይ ማሳያው በቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ የርክበ ካህናት ስብሰባ ላይ “ሊቃነ ጳጳሳት ለአንድ ብሔር ብቻ” ይሾሙ በማለት መንፈሳዊነት የሌለው፤ ከሐዋርያት አስተምህሮና ቀኖና ውጭ ለተግባራዊነቱም ከፍተኛ እንቅስቃሴ እየተካሄደ መሆኑ ነው ብሏል።

አካሄዱም ሐዋርያዊት ብለን የምናምንባትን ቤተ ክርስቲያን የፖለቲካ ሃሳብ ማስፈጸሚያ ከማድረግ አልፎ ቤተ ክርስቲያኒቱን እና ሃገራችንን የሚያጠፋ ነው ሲል አውግዞታል።

መንግሥት ቤተ ክርስቲያኒቱ በሰላም እንዳትተዳደር በቅዱስ ሲኖዶስ መንፈሳዊ አስተዳደር ውስጥ ጣልቃ በመግባት፣አገልጋይ ካህናቷን፣ ሊቃውንቷን እና ምእመናኗን በመግደል፣ በማሰር እና በማሰቃየት መከራ እያጸናባት ነው የመጨራሻ ግቡም ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያንን ከምድሪቱ ላይ ማጥፋት ብሎም ኢትዮጵያ የምትባል ሃገርን መበተን ነው ብሏል የሰሜን አሜሪካ የካህናትና የምእመናን ኅብረት በመግለጫው።

በመሆኑም:_

1- መንግሥት በቤተ ክርስቲያን ላይ ብሎም በንጹሃን ዜጎች ላይ እያደረሰ ያለው በደል የከፋ ከመሆኑ ባሻገር ይህ የቤተክርስቲያንን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥል ነውና ጉዳዩን ለዐለም ማህበረሰብ ለማሳወቅ በቅርቡ ዐለም አቀፍ ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚጠራ፣

2- መንግሥት ቤተ ክርስቲያንን በመከፋፈል ሃይማኖትን የማጥፋት ሃገርንም የመበተን ስራ በከፍተኛ ደረጃ እየሰራ ነው።

ይህ ደግሞ በቀጣይነት የማያቋርጥ የእርስ በእርስ ግጭት ፤የደም መፍሰስ እና ግድያ የሚያመጣ፤ ምስራቅ አፍሪካን ብሎም መላው ዓለምን ከፍተኛ ሥጋት ላይ የሚጥል በመሆኑ ይህንን ጉዳይ ለዐለም አቀፍ ተቋማት ለማሳወቅ፣

3- ከአሜሪካን የሕግ አውጪ አካላት ጋር በሃገሪቱ ባለ ስልጣኖች ላይ የመጓጓዝ ማእቀብ እንዲጣል ብሎም በዐለም አቀፍ ፍርድ ቤት ሃገሪቱ ውስጥ በመንግሥት እየተካሄደ ላለው ግፍ ግድያ እና እንግልት የመንግሥት ባለስልጣናት እንዲጠየቁ የሚሰራ መሆኑን አስታውቋል።