Get Mystery Box with random crypto!

'የኢትዮጵያ ህዝብ የሚመጥነውን የፖለቲካ መሪ በማጣቱ፣ አካታችና ሁሉን አቀፍ ሥርዓት በመነፈጉ እን | አማራ ሚዲያ ማዕከል Amhara media center

"የኢትዮጵያ ህዝብ የሚመጥነውን የፖለቲካ መሪ በማጣቱ፣ አካታችና ሁሉን አቀፍ ሥርዓት በመነፈጉ እንዲሁም በመከዳቱ ባለፉት አምስት ዓመታት በታሪኩ አይቶት የማያውቀውን አስቸጋሪ ጊዜ በማሳለፍ ላይ ይገኛል።"

እናት ፓርቲ

የአማራ ሚዲያ ማዕከል (አሚማ)
ሚያዚያ 24/2015 ዓ/ም
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ

በወቅታዊ ጉዳይ ከእናት ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ:-

"ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ..." ይገባል!

የኢትዮጵያ ህዝብ የሚመጥነውን የፖለቲካ መሪ በማጣቱ፣ አካታችና ሁሉን አቀፍ ሥርዓት በመነፈጉ እንዲሁም በመከዳቱ ባለፉት አምስት ዓመታት በታሪኩ አይቶት የማያውቀውን አስቸጋሪ ጊዜ በማሳለፍ ላይ ይገኛል።

የፖለቲካው መስመር መሳትና ተለዋዋጭነት፣ የውስጥና የውጭ ኃይሎች ቀጠናዊ ፍላጎት፣ ስሁት የጎሰኝነት ትርክቶች፣ መዋቅራዊና ሥርዓታዊ ችግሮች ወዘተ. ህዝባችንን ማብቂያ በሌለው መከራ ውስጥ እንዲኖር አድርጎታል።

በተለይም ባለፉት ሁለት ዓመታት በሕወሓት እና በፌደራል መንግስቱ መካከል የተደረገው ደም አፋሳሽ ጦርነት እና በምዕራብና ማእከላዊ ኦሮሚያ መንግሥት “ኦነግ ሸኔ” ብሎ በሚጠራው ቡድን በንጹሐን ላይ ሲፈፀም የዘለቀው ጅምላ ጭፍጨፋ ኢትዮጵያዊያንን በማይሽር ጥልቅ ሐዘን ውስጥ እንዲወድቁ አድርጓቸዋል።

ከላይ የጠቀስነውና ብዙ ሺህዎች ውድ ሕይወታቸውን ያጡበት የግድያ አዙሪት ቀጥሎ በቅርብ ጊዜያት በምሥራቅ ወለጋ ነቀምቴ፣ በሰሜን ሸዋ ጓሳ እንዲሁም በደቡብ ኦሞ የገዥው ፓርቲ አመራሮች፣ የመንግሥት ተሿሚዎች እና አጃቢዎቻቸው ሕይወታቸውን አጥተዋል።

እነዚህ ግድያዎች በዓላማም ይሁን በሴራ ይፈጸሙ የዜጎች ሕይወት ጠፍቷል።

ግድያውን ተከትሎ አስቀድሞ ጣት የመቀሳሰር ሁኔታዎችን በማቆም ተገቢው ምርመራ ተደርጎ እንደ ዜጋ ፍትህ ሊሰጣቸው እንደሚገባ እናት ፓርቲ በጽኑ ያምናል፡፡ ለሟች ቤተሰቦችም መጽናናትን ይመኛል።

ከዚህ ውጭ ምርመራ ባልተካሄደበትና ጥፋተኞች በአግባቡ ባልተለዩበት ሁኔታ የሚደረጉ ፍረጃዎች የፍትህ አሰጣጡን በእጅጉ እንደሚያዛቡ መረዳት ያስፈልጋል።

መንግስት በቅርቡ የፕሪቶሪያን ስምምነት መሠረት አድርጎ (ምንም እንኳ በስምምነቱ የተጠቀሱት ነጥቦች ባይሟሉም) ከሕወሓት ጋር የሰላም ስምምነት ላይ መድረሱን አሳውቋል።

በጦርነቱ ውድ ሕይወታቸውን ያጡ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች እንደዋዛ ተረስተው የግጭቱ ዋና መሐንዲሶች ሲሸለሙ አገርም ዓለምም ታዝቧል።

ከዚህ በተጨማሪ ችግሮች የከፋ አደጋ ሳያደርሱ በፊት እንደ አግባቡ በጠረጴዛ ዙሪያ መፍታት ባለመቻሉ እንደ አገር ከላይ የጠቀስናቸውን ኪሳራዎች አስተናግደናል። ይህም መንግስት ምን ያህል አክሳሪ የፖለቲካ አካሄድ እየተከተለ እንደሚገኝ ያሳያል።

የውይይት ሂደቱ ያለበት ደረጃ ባይታወቅም፤ መንግስት ሚያዚያ ፲፯/፳፻፲፭ ዓ.ም ከ"ሸኔ" አሸባሪ ቡድን ጋር ድርድር ለማድረግ ታንዛኒያ (ዛንዚባር) ላይ ቀጠሮ መያዙንና ድርድር መጀመሩም ይፋ ከሆነ ሰንብቷል።

ስለሆነም፡-

፩. ካለ ፍትሕ ሰላምን ማስፈን አስቸጋሪ መሆኑን ብናምንም ድርድሩ ከተለመደው የሴራ ፖለቲካ በጸዳ መልኩ ተከናውኖ በስቃይ ውስጥ የሚገኘውን ሕዝባችንን ሊታደግ በሚችል መልኩ እንዲቋጭ እንመኛለን፡፡

መንግስት ለሀገራችን ኢትዮጵያ የሚጠቅም ሀሳብ ካላቸው ፓርቲዎች ጋርም የጋራ መግባባትን ለማስፈን የሚያስችል ውይይት እንዲያደርግም ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።

፪. የአማራ ክልል ብልጽግና ኃላፊ ግድያን ተከትሎ መንግስት አሁንም "ኢ-መደበኛ አደረጃጀቶች"ን ትጥቅ በማስፈታት "ሰላም አስከብራለሁ" በሚል በአማራ ክልል የጀመረው እንቅስቃሴ ከሕወሓትና “ኦነግ ሸኔ” ጋር የታለፈበትንና አገርን ውድ ዋጋ ያስከፈለ አካሄድ የሚደግም ነው፡፡

መንግስት ካለፈ ስህተቱ መማር ሲገባው ወደ ሌላ የግጭት አዙሪት አገርንና ሕዝብን የሚከት፤ የክልሉን ወጣት ለአመጽ የሚጋብዝ፣ በዚህም ከቀደሙት መደበኛ ጦርነትና የሽምቅ ውጊያ ሂደቶች ትምህርት ያልወሰደ፣ የሚያስከትለውንም መጠነ ሰፊ ጉዳት እና መዘዝ በአግባቡ ያላገናዘበ አደገኛ የማንአለብኝነት አካሄድ እየተከተለ መሆኑን እናት ፓርቲ ያምናል።

ስለዚህ ከጀመረው የጅምላ እስር፣ የትጥቅ ማስፈታት ዘመቻ፣ የድርጅቶችን የንግድና የገንዘብ እንቅስቃሴ የማገድ ሂደት ወዘተ. በእሳት ላይ ቤንዚን የማርከፍከፍ አካሄዶች ራሱን አቅቦ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ ሊፈቱ በሚችሉበት ሁኔታዎች ላይ ብቻ እንዲያተኩር አጽንዖት ሰጥተን እናሳስባለን።

፫. አበው "ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ…" እንዲሉ ከዚህ ውጭ የድርድርና የውይይት ፍኖትን ባለመሻት መንግሥት በማንአለብኝነት አካሄዱ ቀጥሎ በአገርና በሕዝብ ላይ ለሚደርሰው ማንኛውም ዓይነት ጥፋትና ውድመት ከተጠያቂነት እንደማያመልጥ እናት ፓርቲ በጽኑ ያምናል።