Get Mystery Box with random crypto!

ልዩ ሀይሉን ወደ መረጠውና ወደ ተመደበበት እያንቀሳቀስን ነው -ዶ/ር ሰማ ጥሩነህ የአማራ ክልል | አማራ ሚዲያ ማዕከል Amhara media center

ልዩ ሀይሉን ወደ መረጠውና ወደ ተመደበበት እያንቀሳቀስን ነው -ዶ/ር ሰማ ጥሩነህ

የአማራ ክልል “ወደ መደበኛ የክልል ፖሊስ ስራ እንገባለን” ያሉ የአማራ ልዩ ኃይል አባላትን፤ በክልሉ ወደሚገኙ ዞኖች መድቦ እያንቀሳቀሰ መሆኑን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ የአስተዳደር ጉዳዮች ክላስተር አስተባባሪ የሆኑት ዶ/ር ሰማ ጥሩነህ ተናገሩ። “በመደናገር” ወደ ተለያዩ አካባቢዎች “የተበተኑ” የልዩ ኃይል አባላትን የሚያሰባስቡ ግብረ ኃይሎች በዞን እና ወረዳ ደረጃ መቋቋማቸውን አስተባባሪው ገልጸዋል።

ዶ/ር ሰማ ይህን የገለጹት፤ በአማራ ክልል ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ ለክልሉ ቴሌቪዥን ጣቢያ ትላንት ረቡዕ ሚያዚያ 4፤ 2015 በሰጡት መግለጫ ነው። የትላንቱ የዶ/ር ሰማ ማብራሪያ፤ የክልል ልዩ ኃይሎችን “እንደገና ለማደራጀት” በፌደራል መንግስቱ የተወሰነው ውሳኔ እና የአማራ ክልል ልዩ ኃይል አባላት የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ ዋና ትኩረቱን ያደረገ ነበር።

የክልል ልዩ ኃይሎችን በተመለከተ የተላለፈው ውሳኔ “በሁሉም ክልሎች እየተፈጸመ ነው” ያሉት ዶ/ር ሰማ፤ “ይሄ ባለበት ሁኔታ የአማራ ክልልን ልዩ ኃይል ብቻ ባለበት እንዲቆይ ማድረግ፣ ወደ ፌደራል ጸጥታ ተቋማት እንዳይገባ መከልከል የሚቻል አይደለም” ሲሉ ተደምጠዋል።

የአማራ ክልል ይህን ውሳኔ ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ ባደረገበት ወቅት፤ በሁለት ምክንያቶች “ችግሮች” ማጋጠማቸውን ዶ/ር ሰማ በትላንቱ ማብራሪያቸው አንስተዋል። ዶ/ር ሰማ ለችግሮቹ መፈጠር በቀዳሚነት የጠቀሱት፤ ከክልሉ ልዩ ኃይል አባላት ጋር “ቀድሞ ውይይት ተደርጎ፣ በቂ መግባባት በማድረግ ረገድ፣ የተፈጠረ ክፍተትን” ነው። ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ፤ ዶ/ር ሰማ “ብጥብጥ እና አመጽ በማስነሳት ስርዓት የመቀየር ፍላጎት ያላቸው” ሲሉ የገለጿቸው “ኃይሎች” ፈጠሩት ያሉት “የውሸት ፕሮፓጋንዳ” ነው።

በዚህ ፕሮፓጋንዳ ምክንያት “የተበተኑ” የልዩ ኃይል አባላት መኖራቸውን የአማራ ክልል የአስተዳደር ጉዳዮች አስተባባሪው ገልጸዋል። እነዚህን “ተደናግጠው” እና “በመደናገር” ተበተኑ የተባሉትን የአማራ ክልል ልዩ ኃይል አባላት የሚያሰባስብ ግብረ ኃይል፤ በክልሉ ስር በሚገኙ ወረዳ እና ዞኖች እንዲቋቋም መደረጉን ዶ/ር ሰማ በትላንቱ ማብራሪያቸው አስታውቀዋል።