Get Mystery Box with random crypto!

ሰከን ብሎ በማሰብ እንጂ ሀገርን ወደ ቀውስ በመግፋት ስልጣንን ማጽናት አይቻልም! የአማራ ሚዲያ | አማራ ሚዲያ ማዕከል Amhara media center

ሰከን ብሎ በማሰብ እንጂ ሀገርን ወደ ቀውስ በመግፋት ስልጣንን ማጽናት አይቻልም!

የአማራ ሚዲያ ማእከል
ሚያዚያ 3 2015 ዓ/ም
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ

በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከእናት ፓርቲ፣ ከመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እና ከኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) የተሰጠ መግለጫ

ኢትዮጵያ ሀገራችን በብዙ መከራ ውስጥ እያለፈች ሲሆን በተለይም በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ኢትዮጵያውያን በሁለት ጎራ ተሰልፈን ባደረግነው ውጊያ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ውድ ሕይወታቸውን አጥተዋል፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን የአካል ጉዳተኞች ሆነዋል፤ ብዙዎች የሥነ ልቡና ስብራት ደርሶባቸዋል፤ ልጆች ያለአሳዳጊ ወላጅ፤ ሚስቶች ያለባል ባሎችም ያለሚስት፣ ወላጆች ያለጧሪ ቀባሪ ቀርተዋል፤ መሰረተ ልማቶች ወድመዋል፤ ሀገራችን በዲፕሎማሲው መስክ ተጽዕኖ እንዲያርፍባት ገጽታዋም በአሉታዊ መልኩ እንዲነሳ አድርጓል፤ ለከፋ የፖለቲካ እና ማኅበረ ኢኮኖሚ ቀውስ ዳርጓታል።

ይህ ኹሉ ከሆነ በኋላ ከነችግሩም ቢያንስ በድርድር ችግሩን ለመፍታት በተደረገው ጥረት ለጊዜውም ቢሆን ጦርነቱ ጋብ እንዲል መደረጉ ጥሩ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ደግሞ ከክልሎች ልዩ ኃይል "ማፍረስ" ጋር በተገናኘ በተለይም በአማራ ክልል ውጥረት ነግሷል፡፡ እንደ ሀገር የኢትዮጵያ ሕዝብ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ምክንያቶች ለርሃብ እና ለከፋ የሕይወት ዉጣ ውረድ የተዳረገ ሲሆን በተለይም የጎሳ ፓለቲካ በወለደው ጽንፈኝነት በሁሉም የሀገራችን ክፍሎች ሕዝባችን ሰላም አጥቷል፤ ነፃነቱን ተነፍጓል፤ በተለይም የአማራ ሕዝብ ርዕዮተ ዓለማዊ ማዕቀፍ ባለዉ ሁኔታ የሐሰት ትርክት ተቀነባብሮበት በጠላትነት ተፈርጆ ላለፉት 32 ዓመታት እንደ ዱር እንስሳ ተገድሏል፣ ተሰድዷል፣ ተፈናቅሏል፣ ንብረቱን ተዘርፏል፣ መኖሪያ ቤቶቹ ፈርሰውበታል ዛሬም ይኸው ተጠናክሮ ቀጥሏል።

እናት ፓርቲ፣ መኢአድ እና ኢሕአፓ ይህን እንደ ሀገር የገባንበትን አደገኛ ሁኔታ በማስወገድ ኹሉም ኢትዮጵያዊ በየትኛውም የሀገራችን ክፍል ያለአድሎ በእኩልነት መኖር እንዲችልና የተረጋጋች ለሁሉም ዜጋ ምቹ ኢትዮጵያን ለመገንባት ከፋፋይ ከሆነው የሕግ መንግስቱን አንቀጾች ማሻሻል ጀምሮ የችግሮቻችን አልፋና ኦሜጋ የሆነውና በጎሳ ላይ የተመሠረተ የፌደራል ሥርዓት ማስተካከል፣ ገለልተኛ የሕዝብ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ማደራጀት ብሎም ከሕግ ውጪ የሆኑ አደረጃጀቶችን ወደ ሕጋዊ መስመር እንዲገቡ ማድረግ አስፈላጊ ነው ብለን እናምናለን፡፡

የክልሎች የልዩ ኃይል አደረጃጀት ኢሕገመንግስታዊና የሀገር የጸጥታ ስጋት ስለሆነ የሀገራችንን ዳር ድንበራችን የሚያስከብር አንድ ጠንካራ መከላከያ ሰራዊት፣ ውስጣዊ የጸጥታ ችግሮች እንዳይፈጠሩ የሚያደርግ የፌደራል ፖሊስ እና ክልሎች ደግሞ መደበኛ ፓሊስ ብቻ እንዲኖራቸው ሊደረግ እንደሚገባ በማመን ይህን አቋም ግልጽ በሆነ ሁኔታ በምርጫ ዘመቻ ወቅት ጭምር ስናንጸባርቅ እንደ ነበር ይታወሳል፡፡

አገር በጎሳ ተከፋፍላ ከፍተኛ ደም አፋሳሽ ጦርነት ባስተናገደችበት ሁኔታ ክልሎች ልዩ ኃይልን እንደ ህልውና ማረጋገጫ እየወሰዱ እንዳሉ በግልጽ ይታወቃል፡፡ ለዋቢነት ህወሃት የአማራን ክልል በወረረበት ወቅት የክልሉ ልዩ ኃይል የተጫወተው ሚና፤ ሕወሃት በተመሳሳይ መልኩ የአፋርን ክልል በድጋሚ በመውረር ሰፊ አካባቢን በተቆጣጠረበት ወቅት የክልሉ ልዩ ኃይል ያለ መከላከያ ሠራዊት ድጋፍ ብቻውን ክልሉን ከህወሃት ነፃ ለማውጣት ያደረገውን ተጋድሎ፤ በቅርቡ አልሸባብ በሶማሌ ክልል በኩል አገራችን ላይ በሰነዘረው ጥቃት የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል የሶማሌን ክልል ሳይሆን የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ግዛት ለማስከበር ያደረገው ተጋድሎና የፈጸመው ጀብድ በጥቂቱ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

የትብብሩ አባል ፓርቲዎች የክልል ልዩ ኃይል አላስፈላጊነት ላይ ወጥ የሆነ አቋም ያላቸው ሲሆን መፍረሱና በልዩ መልኩ ማደራጀት ላይ ከሁሉ አስቀድሞ ለእንደዚህ ዓይነት አደረጃጀት የዳረገውና የጎሳ ፌዴራል ሥርዓትን የደነገገው ሕገ መንግሥት ተለውጦ አገር ከጎሳ አደረጃጀት ስትላቀቅ መሆኑን ያምናሉ፡፡ ይህን ማድረግ ደግሞ የአገራዊ ምክክርና የአገራዊ መግባባት ውጤት ሲሆን አገር ያዝ ለቀቅ እያደረገች የምትከተለው አገራዊ መግባባት ሊከናወን ከቻለ ይህን ተከትሎ በሚለወጠው የጎሳ አደረጃጀትና የህገ መንግሥት ማሻሻያ የክልል ልዩ ኃይሎች ተፈጥሯዊ በሆነ መልኩ እንደሚከስሙ ወይም እንዲከስሙ ማድረግ እንደሚገባ እምነታችን ነው፡፡

አካሄዱ ከላይ እንደገለጽነው መሆን ሲገባ ከሰሞኑ የአማራ ክልልን ልዩ ኃይል ግልጽነት በጎደለው ሁኔታ "በአንድ በኩል ልዩ ኃይል ለማፍረስ በሚመስል መልኩ፣ በሌላ በኩል ደግሞ መልሶ ለማደራጀት" ነው በሚል የተምታታ አገላለጽና ይህንኑ ተከትሎ ልዩ ኃይሉ በእጁ ያሉትን መሣሪያዎች ወደ ግምጃ ቤት እንዲያስገባ በጽሑፍ ትዕዛዝ ከመተላለፉ ጋር ተያይዞ በክልሉ ከፍተኛ ውጥረት ነግሷል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች በከባድ መሣሪያ ጭምር የታገዘ ጥቃት በፀጥታ ኃይሎች እየደረሰ እንደሆነ ለመገንዘብ ችለናል፡፡ የክልሉ ሕዝብ “ከፍተኛ የጸጥታ ስጋት እንዳለብን እየታወቀ እስከአሁን እልባት ያላገኙ የማንነት ጥያቄዎች መልስ ባላገኙበት፣ ሕወሀት ለጦርነት ዝግጅት እያደረገ ባለበት ሁኔታ፣ የሰላም ስምምነቱ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ባልሆነበት፣ ከዚህ በኋላ ሕዝባችንን ለመከራ የሚዳርግ ቀውስ እንደማይፈጠር መተማመኛ ባልተደረሰበት፣ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ባልተፈጠረበት ሁኔታ እና በተለየ መልኩ ከሁሉ ክልሎች በፊት የአማራ ክልልን ልዩ ኃይል ትጥቅ ለማስፈታት የፌደራል መንግሥቱ የጀመረው እንቅስቃሴ ስጋት ፈጥሮብናል“ በሚል ድርጊቱን አየተቃወመ ይገኛል፡፡

አካሄዱ በዚህ መልክ ከቀጠለ አገራችንን ወደ ሁለንተናዊ ቀውስ የሚያስገባ መሆኑ ታውቆ ሕዝባዊ ተቃውሞው ከዕለት ወደዕለት እየተባባሰ ከፍተኛ ውጥረት እየፈጠረ ባለበት በአሁኑ ወቅት የፌዴራል መንግሥት የጀመረውን አካሄድ ቆም ብሎ በአስቸኳይ በመመርመር አገርን ወደ ቀውስ ከመግፋት ተቆጥቦ ሰከን ብሎ ችግሮችን በማጤን የተጀመረው የጥፋት ጉዞ እንዲገታ የትብብሩ አባል ፓርቲዎች አጥብቀን እንጠይቃለን፡፡ ይህንኑ አስመልክቶ፡-
የፌደራል መንግሥቱ ከሚያደርገው ግብታዊ እና ስሜታዊ እንቅስቃሴ በመቆጠብ ነገሮችን በሰከነ ሁኔታ በመመልከት ቀደም ሲል የጠቀስነው አገራዊ ምክክር ተደርጎ ህገ መንግሥታዊ ማሻሻያ እስኪደረግ አገርን ወደ ሁለንተናዊ ቀውስ እየከተተ ያለውን አካሄድ እንዲያቆም አጥብቀን እንጠይቃለን፡፡ አያይዘን መንግሥት ከሴራ እና ሕዝብን ከሚያስቆጡ እንቅስቃሴዎች እንዲቆጠብ እያሳሰብን ይህ ሳይሆን ቀርቶ አገር በዚህ መልኩ ቀጥላ ሊከሰት ለሚችለው ሁለንተናዊ ቀውስ የፌደራል መንግሥቱ ተጠያቂ እንደሚሆን እናሳስባለን።

ሕዝባችን እንደወትሮው ሁሉ አንድነቱን አጠናክሮ ነገሮችን በሰከነ ሁኔታ እንዲመለከት አገርን የበለጠ ጉዳት ላይ ከሚጥሉና ሕዝባችንን እርስ በርስ ከሚያጋጩ አካሄዶች፤ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ መሰረተ ልማቶች እንዲሁም የግልም ሆነ የአገር ሀብት ላይ ጉዳት ከማድረስ በእጅጉ እንዲቆጠብ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።

ፈጣሪ ሀገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ

እናት ፓርቲ፣ መኢአድ እና ኢሕአፓ
ሚያዝያ ፫ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ