Get Mystery Box with random crypto!

በሌላ በኩልና በዋናነት የአማራ ሕዝብ ወደ ሀገሩ መዲና አዲስ አበባ በነፃነት መግባትና መውጣት የማ | አማራ ሚዲያ ማዕከል Amhara media center

በሌላ በኩልና በዋናነት የአማራ ሕዝብ ወደ ሀገሩ መዲና አዲስ አበባ በነፃነት መግባትና መውጣት የማይችልበት ሁኔታ ተፈጥሯል። በአጠቃላይ በአዲስ አበባና አጎራባች አካባቢዎች፣ በተለይም ሸገር ከተማ ተብሎ በተዋቀረው አካባቢ በሚኖረው ሕዝብ ላይ የመንግስት አካላት በማንነት እየለዩ መኖሪያ ቤቶችን በማፍረስና ንብረቶችን በመዝረፍ በርካታ ቤተሰቦችን ሜዳ ላይ እየበተኑት ይገኛል። ሕዝባችን ሀገር አልባና መንግስት አልባ የሆነበት ሁኔታ ተፈጥሯል። የአማራ ሕዝብ በዋናነት በትሕነግ እና በኦነግ-ሸኔ ከተከፈቱበት የጥፋት ዘመቻዎች በተጨማሪ በትሕነግ የተሰማራውና ድጋፍ በሚደረግልላቸው የውስጥ ሽብርተኞች ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል። በአሁኑ ወቅት የአማራ ሕዝብ ከላይ በተጠቀሱት የሽብር ኃይሎች በኩል የሚፈፀሙበት ጥቃቶች የቀጠሉ ሲሆን ወደፊትም ተጨባጭ ስጋቱ እንደሚቀጥል መገመት አያዳግትም። የአማራ ሕዝብ በጦርነቱ ምክንያት ከደረሰበት ጉዳት ገና አላገገመም። ለኅልውና ዘመቻ በነፍስወከፍ ሀገራዊ ጥሪ የተደረገለት ሕዝብ ድህረ ጦርነት ይህ ነው የሚባል የመልሶ ማቋቋም ድጋፍ አልተደረገለትም። የአማራን ሕዝብ መልሶ ማቋቋም የችሮታ እና የግብረሰናይ ጉዳይ ተደርጎ ተወስዷል።

ስለሆነም ከላይ በዝርዝር የገለፅናቸውን ተጨባጭ የሆኑ ነባራዊ ሁኔታዎች ከግምት ውስጥ በማስገባት ፖርቲያችን የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ የገዥው ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ የአማራ ልዩ ኃይልን ለማፍረስ እና ትጥቅ ለማስፈታት ያሳለፈው ውሳኔ እና የሚያደርገው እንቅስቃሴ ኃላፊነት የጎደለውና ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ድጋሜ ማሳወቅ ይፈልጋል። ቀደም ሲል በዝርዝር እንደገለፅነው የብልፅግና ፖርቲ ሥራ አስፈፃሚ የአማራ ልዩ ኃይልን ለማፍረስና ትጥቅ ለማስፈታት ያሳለፈው ውሳኔ መሬት ላይ ያለውን ሃቅ ያላገናዘበ ፣ መርኅ አልባ ፣ አድሏዊ እና አምባገነናዊ ነው፡፡ ውሳኔውና የአፈፃፀም ሂደቱ በሕግ አግባብ የተመራ ፣ መርኅ ተኮር እንደሆነ ፣ ውይይት እንደተደረገበት እና መግባባት የተደረሰበት እንደሆነ ለማስመሰል የሚቀርቡ አስተያየቶች በአጠቃላይ ሃሰት ናቸው።

1. የአማራ ልዩ ኃይል አመራሮች፣ አባላት እና በአጠቃላይ የአማራ ሕዝብ አልተወያየም፣ ፍፁም የሚያውቀው ነገር አልነበረም።

2. በየአካባቢው ተመድበው ስምሪት ላይ የነበሩ የአማራ ልዩ ኃይል አደረጃጀቶችና አባላት ስለጉዳዩ ምንም አይነት መረጃ አልነበራቸውም። በስምሪት እና በካምፖች ውስጥ ባሉበት ወቅት እንደጠላት ተቆጥረው በኃይል እና በከበባ ትጥቃቸውን የመቀማትና የመበተን ሙከራ ተደርጓል። ሰሞኑን በአማራ ልዩ ኃይል ላይ የተፈፀመው ድርጊት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ትሕነግ በሀገር መከላከያ ሠራዊት ሰሜን እዝ ላይ ከፈፀመው ከበባና ጥቃት ጋር ተመሳሳይነት ያለው ክብረ ነክ አዋራጅ ድርጊት ነው።

3. የአማራን ሕዝብ ተወቃሽ የማድረጉ ጥረት በየመድረኩ ቀጥሏል። በሕዝብ እንደራሴ ምክር ቤት ፊት ሳየቀር ለትሕነግ ጠበቃ ሆነው የአማራን ህዝብ ለመዝለፍ የሚዳዳቸው የመንግስት ባለስልጣናትን ተመልክተናል።

4. ሌሎች ክልሎች ነባራዊ የሰላም ሁኔታቸውን ታሳቢ እያደረጉ መወሰን ይችላሉ። ሆኖም የአማራ ልዩ ኃይል አሁን ትጥቁን የማይፈታባቸው የራሱ በቂ ምክንያቶች እንዳሉት ከላይ በዝርዝር አስረድተናል። ከአውድ ውጭ ለማነፃፀር መሞከር በራሱ ሚዛን አልባነት ነው።

5. ከላይ የተገለፀው እንደተጠበቀ ሆኖ የትሕነግ ኃይል በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሰረት ትጥቁን አልፈታም፤ እንዲያውም ተጨማሪ ኃይል እየመለመለ እና እያሰለጠነ፣ እያስታጠቀ እና የውጊያ ልምምዶችን እያደረገ አዲስ የጦርነት ዝግጅት ላይ መሆኑን መንግስት ጠንቅቆ ያውቃል። ዝግጅቱ የሚደረገው በትግራይ ውስጥ እና ከትግራይ ውጭ በጎረቤት አገር ሱዳን ጭምር ነው። ስለሆነም በመንግስት በኩል ከዚህ በተቃራኒ ትሕነግ ትጥቅ እንደፈታና በአካባቢው የሰላም ድባብ እንደሰፈነ የሚወራው ሀሰት ነው።

6. በፌዴራል መንግስቱ ይሁንታ የተቋቋመው የትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደር የፌዴራል መንግስቱ የራያና የወልቃይት የአማራ አካባቢዎችን ክረምት ሳይገባ እንደሚያስረክባቸው በትግርኛ ቋንቋ በሰጡት ቃለ መጠይቅ በይፋ ገልፀዋል። በርካታ የትግራይ ፖለቲከኞች አጋጣሚውን በመጠቀም ድጋሜ ወረራ ለመክፈት የሚታወቅ ውይይትና ዝግጅት እያደረጉ ይገኛሉ። በመጨረሻ ይህ ጉዳይ ከፍተኛ አለመረጋጋት የሚፈጥር እና ሌላ የቀውስ አዙሪት ውስጥ የሚያስገባን አደገኛ አካሄድ በመሆኑ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ለገዥው የብልፅግና ፓርቲ ፣ ለፌዴራሉ መንግስት ፣ ለአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት እንዲሁም ለሁሉም የክልል መስተዳደሮች በጥብቅ ለማሳሳብ ይወዳል፡፡

በመሆኑም የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ የሚከተሉትን ጥሪዎች ያስተላልፋል:-

ሀ. የፌዴራሉ መንግስት ውሳኔውን እንደሰረዘ በአደባባይ እንዲገልጽ እና የአማራ ልዩ ኃይል አባላት እና የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ወደ ካምፓቻቸው እና ወደ ግዳጅ ቦታቸው እንዲመለሱ በይፋ ጥሪ እንዲያደርግ፤

ለ. በፌዴራል መንግስቱ ውሳኔ እና ትዕዛዝ ከሥራ ውጭ የሆኑት የአማራ ልዩ ኃይል የብርጌድ እና የክፍለ ጦር አዛዞዦች ወደምድብ ቦታቸው እንዲመለሱ እንዲደረግ፤

ሐ. የአማራ ክልል መንግስት ለልዩ ኃይሉ አስፈላጊ የሆኑ ስንቅ እና ሎጂስቲክ እንዲያቀርብ እና ደሞዝ እንዲከፍል፤

መ. በካምፕ እና በግዳጅ ቦታችሁ ላይ የምትገኙ ውድ የአማራ ክልል የልዩ ኃይል ፖሊስ አመራሮች እና አባላት ሠራዊቱ እንዲበተን የሚደረጉ ጥረቶችን እና የፕሮፖጋንዳ ጥቃቶችን በመቋቋም በተለመደው ሥነ-ምግባር ፣ ዲስፕሊን እና ጨዋነት ከህዝባችሁ ጎን እንድትቆሙ፤

ሠ. የአማራ ሕዝብ በያካባቢው ላሉት የልዩ ኃይል አባላት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ድርጅታችን ጥሪውን ያቀርባል።

አብን ጉዳዩን በቅርበት እና በንቃት እየተከታተለው መሆኑን እና በቀጣይም ሁኔታዎችን እየገመገመ ተከታታይ አቅጣጫዎችን የሚያስቀምጥ መሆኑን እየገለጸ መላው የአማራ ሕዝብ እና ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ከሀገር ወዳዱ የአማራ ልዩ ኃይል ጎን እንድትቆሙ የከበረ ጥሪውን ያቀርብላችኋል።

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)
አዲስ አበባ ፣ ሸዋ ፣ ኢትዮጵያ
ሚያዚያ 1 ቀን 2015 ዓ.ም