Get Mystery Box with random crypto!

አሳዛኝ ዜና! ከምስራቅ ወለጋ ኪረሞ ወረዳ ተነስተው ለህክምና ወደ አማራ ክልል በእግራቸው እየተጓ | አማራ ሚዲያ ማዕከል Amhara media center

አሳዛኝ ዜና!

ከምስራቅ ወለጋ ኪረሞ ወረዳ ተነስተው ለህክምና ወደ አማራ ክልል በእግራቸው እየተጓዙ የነበሩ 5 አማራዎች በአሸባሪ ኦነጋዊያን በግፍ ተገደሉ።

አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ
መጋቢት 23 ቀን 2015 ዓ/ም
አዲስ አበባ ሸዋ

አማራዎች በማንነታቸው ተለይተው በአሰቃቂ መልኩ በተደጋጋሚ ከተጨፈጨፉባቸው በዋናነት 9 የኦሮሚያ ዞኖች መካከል የምስራቅ ወለጋ ዞን አንደኛው ነው።

በምስራቅ ወለጋ ዞን በሁሉም ወረዳዎች በሚባል ሁኔታ አሸባሪ እና ወራሪ ኦነጋዊያን ከመንግስት አካላት ጭምር በስንቅ፣በትጥቅ እና በመረጃ እየተደገፉ ተደጋጋሚ አማራ ተኮር ፍጅት፣ የማፈናቀል እና ዩየማሳደድ አስከፊ ወንጀል ፈጽመዋል።

ከእነዚህ ወረዳዎች መካከል አንዱ የሆነው ኪረሞ በኦሮሞ ልዩ ኃይል በማንነታቸው የታሰሩ ሴቶች፣ህጻናት እና አቅመ ደካሞች ጭምር በግፍ ተገድለዋል።

መጋቢት 19/2015 ከንጋቱ 12 ሰዓት ገደማ ጀምሮ ከኪረሞ ወረዳ ሀሮ አዲስ ዓለም እና ከባጊን ቀበሌ ተነስተው ለህክምና ወደ አማራ ክልል በእግራቸው እየተጓዙ የነበሩ 5 አማራዎች በአሸባሪ ኦነጋዊያንን በግፍ ተገድለዋል።

እነዚህ እድሜያቸው ከ35 እስከ 50 ዓመታት የሆኑት አማራዎች ለህክምና በሚል በአባይ በርሃ በኩል ጫካ ለጫካ እየሄዱ ባሉበት አባይ ወንዝ እንደደረሱ በአሸባሪ እና ወራሪ ኦነጋዊያን ተይዘው አረመኔያዊ በሆኑ መልኩ በጥይት እና በስለት ተወግተው ተገድለዋል።

በግፈኞች የተገደሉት አማራዎችም:_

1) አቶ ክንዱ አምሳሉ፣
2) አቶ ፈንታልጅ አቸነፍ፣
3) አቶ ሲሳይ ነጋሽ፣
4) አቶ መሀመድ ሀሰን እና
5) ወ/ሮ ሰርኬ ተገኘ የተባሉ የኪረሞ ነዋሪዎች ሲሆኑ በተለይም ወ/ሮ ሰርኬ ተገኘ እና አቶ መሀመድ ሀሰን እናት እና ልጁ አንድ ላይ የመገደላቸው መራር ዜና ብዙዎችን አሳዝኗል።

በወቅቱም የታመሙትን እናት ወ/ሮ ሰርኬን እየደገፉ ወደ አማራ ክልል በመውሰድ ለማሳከም እና አስቸኳይ የሰብአዊ እርዳታም ለማግኘት በሚል ጭምር በእግር ተጉዘው አባይ ወንዝ ሲደርሱ ነው ከተደበቁበት ጎሬ በመውጣት የገደሏቸው።

በጥይት ከመቱ በኋላም በምሳር እና በቆንጨራ ጭምር ጭንቅላታቸውን እና ሌሎች የሰውነት ክፍሎቻቸውን በመምታታቸው እና በመቆራረጣቸው ለቀብርም አስቸጋሪ እንደነበር ተመላክቷል።

አቶ ክንዱ አምሳሉ፣አቶ ፈንታልጅ አቸነፍ እና አቶ ሲሳይ ነጋሽ ነዋሪነታቸው በኪረሞ ወረዳ ባጊን ቀበሌ ሰጊ ኪዳነ ምህረት በመሆኑ አስከሬናቸው እንዲነሳ ተደርጎ መጋቢት 20/2015 ከቀኑ 6 ሰዓት ገደማ ስርዓተ ቀብራቸው ተፈጽሟል።

የኪረሞ ወረዳ ነዋሪዎች ከነቀምት ወደ ባህር ዳር የሚወስደው የፌደራሉ መንገድ በአሸባሪ ኦነጋዊያን በመንግስት አካላት ትብብር ጭምር ከተዘጋባቸው ሶስት ዓመት ገዳማ እንደሆናቸው ተናግረዋል።

በዚህም ምክንያት በኦሮሞ የመንግስት የጸጥታ አካላት እና በአሸባሪው ኦነግ ሸኔ ቅንጅት በተደጋጋሚ የወረራ ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል፤ በርካታ ሰላማዊ ነዋሪ አማራዎችም ተጨፍጭፈዋል።

አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ እንዳይደርሳቸው ከመደረጉም ባሻገር ወደ ኪረሞም ሆነ ወደ ነቀምት፣ ወደ ጎጃም እና ወደ ሌሎችም አካባቢዎች ተጉዘው እንዳይገበያዩ፣ እንዳይሸጡ፣ እንዳይለውጡ በመዳረጋቸው ለከፍተኛ ሁለንተናዊ ችግር ተዳርገዋል።

የህክምና ተቋም፣ ባለሙያ እንዲሁም መድኃኒት ባለመኖሩ ወላድ እናቶች፣ በተጨማሪም ህጻናት እና በአሸባሪው ኦነግ እና በኦሮሞ ልዩ ኃይሎች የቆሰሉት ነዋሪዎች ህክምና ባለማግኘታቸው በርካቶች እየሞቱ ስለመሆኑ የአካባቢው የመረጃ ምንጮች ለአማራ ሚዲያ ማዕከል (አሚማ) ተናግረዋል።

ከፍተኛ የሆነ የአቅርቦት ችግር እንዳለ የሚናገሩት ነዋሪዎች መከላከያም በአማራዎች ጭፍጨፋ በተፈጸመበት ኪረሞ ከገቡ 3 ወራት የተቆጠረ ቢሆንም ለሀሮ አዲስ ዓለም አማራዎች ሊደርሱከት እንዳልቻሉ ተመላክቷል።

ማዳበሪያ የለም፣ በጸጥታ ችግር የተነሳ ተንቀሳቅሰን ለመስራት ተቸግረናል፣ መውጫ መግቢያ አጥተናል፣ ኑሮ በከፍተኛ ሁኔታ ተወዷል፣ እንደአብነትም አንድ የልብስ ሳሙና እስከ 100 ብር እንዲሁም 5 ሊትር ዘይት ከተገኘ እስከ 1,600 ብር እየገዛን ለመጠቀም ተገደናል ብለዋል።

በመጨረሻም የሚመለከተው አካል ሁሉ በአስቸኳይ ፍትህ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።