Get Mystery Box with random crypto!

ኢጋድ፤ የዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁን ዋና ጸሀፊነት ለተጨማሪ አራት ዓመታት አራዘመ የምስራቅ አፍሪካ | Ahmed Habib Alzarkawi

ኢጋድ፤ የዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁን ዋና ጸሀፊነት ለተጨማሪ አራት ዓመታት አራዘመ

የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) የዋና ጸሀፊው ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁን የስራ ዘመን ለተጨማሪ አራት ዓመታት አራዘመ። የቀድሞው የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በኢጋድ ዋና ጸሀፊነታቸው እንዲቀጥሉ የተወሰነው፤ ዛሬ ሰኞ ሰኔ 5፤ 2015 በጅቡቲ በተካሄደው የድርጅቱ መደበኛ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ነው።

ከመሪዎቹ ውሳኔ በኋላ ዶ/ር ወርቅነህ በይፋዊ የትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ “ጉባኤው በእኔ ላይ ሙሉ መተማመን አሳድሮ የስልጣን ዘመኔን ለሁለተኛ 4 አመት ስላራዘመልኝ ጥልቅ ደስታ ይሰማኛል” ብለዋል። ዶ/ር ወርቅነህ ኬንያዊውን ማህቡብ ማሊምን በመተካት የኢጋድ ዋና ጸሀፊነት ኃላፊ ሆነው የተሾሙት በህዳር 2012 ዓ.ም ነበር።

በዛሬው የኢጋድ ስብሰባ፤ አባል ሀገራት በዙር በሚደርሳቸው የሊቀመንበርነት ኃላፊነት ስልጣን ላይም ለውጥ ተደርጓል። ላለፉት አራት ዓመታት ኢጋድን በሊቀመንበርነት ስትመራ የቆየችው ሱዳን የዛሬውን ጉባኤ ላስተናገደችው ጅቡቲ ኃላፊነቱን አስረክባለች። ኢትዮጵያ  ይህን የኃላፊነት ቦታ ለሱዳን አሳልፋ ከመስጠቷ በፊት ለዘጠኝ ዓመታት ኢጋድን በሊቀመንበርነት መምራቷ ይታወሳል።

በጅቡቲ በተካሄደው በዛሬው የመሪዎች ጉባኤ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ጨምሮ የጅቡቲ፣ ሶማሊያ፣ ኬንያ እና ደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንቶች ተሳትፈዋል። በሱዳን ወቅታዊ ሁኔታ እና በሶማሊያ ጉዳዮች ላይ በዋነኛነት በመከረው በዚህ ስብስባ ላይ፤ ኤርትራ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ኦስማን ሳለህ ተወክላለች።

ኢትዮጵያን ኢንሳይደር