Get Mystery Box with random crypto!

የአፋር ክልል ፕሬዚዳንት ሃጂ አወል አርባ ለ127ኛው የአድዋ ድል የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አ | Ahmed Habib Alzarkawi

የአፋር ክልል ፕሬዚዳንት ሃጂ አወል አርባ ለ127ኛው የአድዋ ድል የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላለፉ...

የአድዋ ድል የአንድነት፣ የጅግንነትና የፅናት ተምሳሌት ነው። አባቶቻችን ሀገር ሊወር የመጣ ወራሪን ከጫፍ እስከ ጫፍ እንደ አንድ ሰው ልብ አንድነታቸውን አጠናክረው፣ ጀግንነትን አንግበው በመሰለፍ በፅናት በመፋለም ጠላት ያልጠበቀው ሽንፈት እንዲከናነብ ማድረግ ችለዋል። የእነሱ ድል ማድረግና አሸናፊነትም በወቅቱ የተጠናቀቀ ድል ብቻ ሳይሆን ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፍ ለመላው ኢትዮጵያውያን፣ አፍሪካውያን፣ ብሎም ለጥቁር ህዝቦችና ለነፃነት ለሚታገሉ ህዝቦች ትልቅ አርአያ ሆኖ ሁሌም እየተገለጠ የሚጠቀስ ዋቢ መፅሀፍ እንዲሆን አድርገው አልፈዋል።

የአድዋ ድል ትልቁ ምስጢር የአባቶቻችን የጠነከረ አንድነት ፣ ሀገርን ያስቀደመ በተግባር የሚገለፅ ጀግንነትና ዓላማን ዳር ለማድረስ የነበራቸው የበረታ ፅናት ነው። ከምስራቅ፣ ከምዕራብ፣ ከደቡብ፣ ከሰሜን 'ሀገሬን' ብሎ የተሰባሰበው በርካታ ልዩነቶችን በማቻቻል ለአንድ አላማ ሀገርን ከወራሪና ከቅኝ ግዛት የማዳን የፀና የሀገር ፍቅርን በማሳየት ውድ የሆነውን የህይወት መስዋእትነት በመክፈል ሀገርን ከነሙሉ ክብሯ ለቀጣይ ትውልድ ማስተለለፍ ችለዋል።

የአድዋ ድል የመላው ኢትዮጵያውያን የጋራ ድል ነው። አባት አርበኞች አድዋ ላይ መስዋእትነት ሲከፍሉ ያለ ሀይማኖት፣ ብሄር ቋንቋና ማንነት ልዩነት በጋራ ነበር። ድሉም ለሆነ አካል ተቆርሶ የሚሰጥ እና ለሌላው የሚከለከል ሳይሆን ሁሉም ኢትዮጵያውያን በጋራ መስዋእት የሆኑለት የጋራ የአሸናፊነት ታሪካችን ነው።

ይህን የጋራ የአሸናፊነት ታሪካችንንም አዲስ ታሪክ ፅፈን ለማለፍ ዋቢ መፅሀፍ በማድረግ በርካታ ቁም ነገሮችን በመቅሰም በርካታ ድሎችን ልናስመዘግብ ይገባናል። ኢትዮጵያችን የተሻለችና የበለፀገች፣ የዜጎቿን የምግብ ዋስትና ያረጋገጠች፣ ሰላማቸው የተጠበቀ ህዝቦች እንድንሆን ሁላችንም በየተሰማራንበት መስክ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ይጠበቅብናል።

አባት አርበኞች ህይወታቸውን በመገበር ነፃነታችንን ማረጋገጥ እንደቻሉት፣ እኛ ደግሞ እውቀታችንን፣ ጊዜያችንን እና ጉልበታችንን በማቀናጀት ከድህነት ራሳችን ነፃ ማድረግ ይኖርብናል። ስራዎቻንን በሙሉ አንድነት እና በህብረት ፣በመተባበር እና በመደጋገፍ ፣ በጀግንነትና ፅናትን በመላበስ ማስኬድ ግድ ይለናል። ድህነትን ማሸነፍ የምንችለው ከፈጣሪ በታች በጋራ እጅ ለእጅ በመያያዝ እውነተኛ የሀገር ፍቅር እና አርበኝበትን በመሰነቅ የአንዳችን እድገትና ብልፅግና የአንዳችን እድገትና ብልፅግና መሆኑን በመገንዘብ በተቃራኒው ደግሞ ውድቀታችን የጋራ መሆኑን ጠንቅቀን በማወቅ ላለመውደቅና ወደ ተሻለ ከፍታና ብልፅግና በህብረት ለመሸጋገር የጀመርናቸውን የልማት ስራዎችን በፅናት ማስቀጠል ይኖርብናል።

የጀመርናቸው የሌማት ትሩፋት ፕሮግራም፣ የስንዴ ልማት፣ የተለያዩ ሜጋ ፕሮጀክቶችና የልማት ስራዎችን ሁሉም ኢትዮጵያዊ በባለቤትነት ስሜት የበኩሉን ግዴታ በመወጣት እንደ አንድ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ አሻራውን ማኖር የዜግነት ግዴታ ነው።

የአድዋ ድል የቅኝ አልገዛም ባይነት፣ የባርነት እና የጭቆና ጠል እንቅስቃሴ ነው። የአሁንም ትውልድ የአባቶቹን ታሪክ በመድገም ለሁሉም ችግሮቹ ሀገር በቀል መፍትሄዎችን መነሻ በማድረግ ችግሮቹን በብልሀትና በጥበብ በመፍታት ከኢትዮጵያችን አልፎ ለአፍሪካ ብሎም ለአለማችን ችግሮች ሁነኛ መፍትሄ ሆኖ ሊገኝ ይገባል።

ለልማት ለእድገትና ለሰላም ጉዞው በየመንገዱ ላይ ለሚያጋጥሙ መሰናክሎችና ጊዚያዊ ችግሮች እጅ ባለመስጠት።

(ኢ.ፕ.ድ)