Get Mystery Box with random crypto!

«አሥሩ የዚልሂጃ ቀናት- ከዱኒያ ቀናቶች ሁሉ በላጮች ከዱኒያ ቀናቶች ሁሉ እጅግ በላጮች የሆኑት | አል ሙስሊም 🌴🌴🌴

«አሥሩ የዚልሂጃ ቀናት- ከዱኒያ ቀናቶች ሁሉ በላጮች

ከዱኒያ ቀናቶች ሁሉ እጅግ በላጮች የሆኑት የመጀመሪያዎቹ አሥሩ የዚልሂጃ ወር ቀናት ናቸው። እነሆ እነኚህ ምርጥ ቀናት ከፊት ለፊታችን ተደቅነዋል። ለዚህም ይመስላል ሙስሊሙ የአላህን ቤት ከዕባን ለመጎብኘት ያለው ጉጉቱ ድንበር አልፏል፤ በከዕባ ዙሪያ ጠዋፍ ለማድረግ፣ በሶፋና መርዋ መካከል ለመሮጥ እና ዐረፋ ላይ ቆሞ አላህን ለመለመን ያለው ስሜት ጣሪያ ነክቷል። የታላቁን ነቢይ መስጅድ መስጅደ-ነበዊን ለመጎብኘትና በመስጅዱ ውስጥ በተከበረው ቦታ ረውደቱ ሸሪፋ ላይ ለመስገድ ያለው መነሣሣት ውስጥን ይነቀንቃል፤ በሀሣብ ያምሣል፣ ክንፍ ቢኖር “ምነዋ ወደዚያ ወደተቀደሰው ምድር በበረርኩ!” ያስብላል።

ወዳጆቼ! እኛስ እነኚህ እጅግ የተባረኩና የተከበሩ ቀናቶች ከያዙት ምንዳ ለመቋደስ ምን ማድረግ እንችል ይሆን?

አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ ዘወትር በትእዛዙ በመገኘት ለቋሚው ሀገራቸው ለሚሰንቁ መልካም ባሮቹ በነኚህ በተባረኩ ቀናት ውስጥ ምን ዓይነት ትልቅ ምንዳ ይሆን ያዘጋጀላቸው?

የዚልሂጃ ወር የመጀመሪያዎቹ አሥር ቀናት ታላቅነት

1. አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላ የማለባቸው ቀናት መሆናቸው

አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ አለ

وَالْفَجْرِ ﴿١﴾ وَلَيَالٍ عَشْرٍ ﴿٢﴾ وَالشَّفْعِ وَالْوَتْرِ ﴿٣﴾

“በጎህ እምላለሁ። በዐሥር ሌሊቶችም። በጥንዱም በነጠላውም።” (አል-ፈጅር 89፤ 1-3)

ከጃቢር ኢብኑ ዐብዱላህ (ረ.ዐ) እንደተዘገበው የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እነኚህ አሥር ቀናቶች የትኞቹ እንደሆኑ በሚያመላክተው ሀዲሣቸው ውስጥ እንዲህ ብለዋል፡-

العشر عشر الأضحى، والوتر يوم عرفة، والشفع يوم النحر

“አሥሩ ማለት አሥሩ የአድሃ ቀናት ናቸው። ‘ወትር’ /ጥንዱ/ የተባለው የዐረፋ ቀን ሲሆን ‘ሸፍዕ’ /ነጠላው/ ማለት ደግሞ የነህር /የእርዱ/ ቀናት ናቸው።” ብለዋል። ሀዲሱን ኢማም ነሣኢ እና ሃኪም በሙስሊም መስፈርት መሠረት ሰሂህ ትክከለኛ ሀዲስ ነው ብለውታል።

ኢማም በይሀቂ ከዐብዱላህ ኢብኑ ዙበይር እንደዘገቡት ደግሞ:-

ليالٍ عشر، العشر الثماني، وعرفة، والنحر

“አሥርቱ ሌሊቶች የመጀመሪያዎቹ ስምንቶቹ፣ የዐረፋ ቀን እና የእርድ ቀን ናቸው።” ብለዋል።

2. እነኚህ ቀናት “አያም መዕሉማት” /የታወቁ ቀናት/ም ይባላሉ

ይህም በሚከተለው የቁርዓን አንቀፅ ውስጥ የተጠቀሠ ነው።

وَيَذْكُرُوا اسْمَ اللَّهِ فِي أَيَّامٍ مَّعْلُومَاتٍ [٢٢:٢٨]

“በታወቁ ቀኖችም ውስጥ የአላህን ስም ያወሱ ዘንድ” (አል-ሀጅ 22፤ 27)

“የቁርዓን ተርጓሚ” በመባል የሚታወቁት ታላቁ ሰሃባ ዐብዱላህ ኢብኑ ዐባስ እነኚህ ቀናት “አሥርቱ ቀናት” ናቸው ያሉ ሲሆን በነኚህ ቀናት ውስጥ ታላቁን ጌታ አላህ ሱብሃነሁ ወተዓላን በብዛት ማውሳት የተወደደ ነው።

3. ከዱኒያ ቀናቶች ሁሉ በላጮቹ

ይህም በሚከተለው ሀዲስ ውስጥ ተነግሯል። ከጃቢር (ረ.ዐ) እንደተዘገበው የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡-

أفضل أيام الدنيا أيام العشر، يعني: عشر ذي الحجة، قيل: ولا مثلهن في سبيل الله؟، قال ولا مثلهن في سبيل الله إلا رجل عفر وجهه في التراب، وذُكر عرفة، فقال يوم مباهاة ينزل الله تبارك وتعالى إلى سماء الدنيا، فيقول: عبادي شعثًا غبرًا ضاحين، جاءوا من كل فجٍّ عميق يسألون رحمتي، ويستعيذون من عذابي ولم يروا، فلم نر يومًا أكثر عتيقًا وعتيقة من النار

“ከዱኒያ ቀናቶች ሁሉ በላጮቹ አስሩ ቀናት ናቸው። ማለትም አሥሩ የዚልሂጃ ቀናት። በአላህ መንገድ ላይ መውጣትም ቢሆን የነሱ አምሣያ የለምን? ተብለው ተጠየቁ። እርሳቸውም ‘በአላህ መንገድ ላይም ቢሆንም እነሱን የሚመስል የለም። ፊቱ ከአፈር የተገናኘ ሰው (በአላህ መንገድ ላይ የሞተ) ሲቀር።’ አሉ። ስለ ዐረፋም ተወሳና መልእክተኛው (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ አሉ ‘እሱ የሙባሃት /አላህ በባሮቹ የሚኩራራበት/ ቀን ነው። አላህ ወደ ቅርቢቱ ዓለም ይወርድና ባሮቼ ተንጨፋረው፣ አቧራ የለበሱ ሆነውና ተጎሣቁለው እሩቅ ከሆነ አቅጣጫ ሁሉ እዝነቴን ሊጠይቁ እሷን ያላዩ ሲሆን ከእሣቴም በኔ ሊጠበቁ መጡ። ወንድም ሆነ ሴት በብዛት ከእሣት ነፃ የሚወጡበት እንዲዚህ ቀን አላየንም’።” (በዛር ሀዲሱን ዘግበውታል)

4. በርካታ የሀጅ ሥራዎች የሚሠሩት በነኚህ ቀናት ውስጥ ነው

ከነኚህም መካከል የዚልሂጃ ስምንተኛ ቀን በሙዝደሊፋ ይታደራል፤ በዘጠነኛው ቀን በዐረፋ ላይ ይቆማል፤ ከዚህም በተጨማሪ ለመስዋእት የሚሆን እንሠሳት መንዳት፣ ጠጠር መወርወር፣ ፀጉር መላጨት አሊያም ማሣጠር፣ በዚልሂጃ አሥረኛው ቀን ጠዋፍ ማድረግንና የመሳሰሉትን ያጠቃልላል።

5. የአምልኮ ዘርፍ የሆኑት ዋና ዋናዎቹ የሚሰበሰቡባቸው ቀናቶች ናቸው

ኢማም ሃፍዝ ኢብኑ ሀጀር ፈትሁልባሪ በተሠኘው ታዋቂ ኪታባቸው ውስጥ እንዲህ ይላሉ

والذي يظهر أن السبب في امتياز عشر ذي الحجة لمكان اجتماع أمهات العبادة فيه، وهي الصلاة والصيام والصدقة والحج، ولا يتأتى ذلك في غيره

“የዚልሂጃ አሥርቱ ቀናትን ለየት ከሚያደርጉ ነገሮች መካከል ቦታው ከአምልኮ ተግባራት ዋና ዋና የሚባሉት በአንድ ላይ ተሰባስበው የሚሠሩበት መሆኑ ነው። ይሀውም ሰላትን፣ ፆምን፣ ሰደቃን (ምጽዋትን) እና ሀጅን ያጠቃልላል። ከነኚህ ቀናት ውጭ እነኚህ ሁሉ ነገሮች አንድ ላይ የሚሰባሰቡበትን አጋጣሚ አናገኝም።” (ፈትሁልባሪ ቅጽ 2፣ ገጽ 462)

በነኚህ ቀናት ውስጥ ከሚወደዱ ሥራዎች መካከል

1. ሐጅና ዑምራ ማድረግ

በነኚህ ቀናት ውስጥ የሚሠሩ ምርጥ የአምልኮ ሥራዎች ናቸው። ምክኒያቱም የነኚህ አምልኮ ሥራዎች ትክክለኛ ወቅቱ ይህ ነውና። ከአቢሁረይራ (ረ.ዐ) እንደተዘገበው የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ)እንዲህ አሉ:-

العمرة إلى العمرة كفارة لما بينهما، والحج المبرور ليس له جزاء إلا الجنة

“አንደኛው ዑምራ እስከ ሌላኛው ዑምራ በመካከላቸው የተሰራ ወንጀልን ያብሣል፤ መብሩር /የተሟላ/ የሆነ ሀጅ ምንዳው ጀነት ብቻ እንጂ ሌላ አይደለም።” (ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል)

2. በበጎ ሥራዎች ላይ መበርታት

ከዐብዱላህ ኢበብኑ ዐባስ (ረ.ዐ) እንደተዘገበው የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ አሉ፡-

ما مِن عمل أفضل من عمل فى هذه الأيام العشر، قالوا: ولا الجهاد؟ قال ولا الجهاد إلا رجل خرج بماله ونفسه فلم يرجع منه بشيء

“በነኚህ አሥር ቀናት ውስጥ የሚሠራ ሥራን የሚበልጥ ምንም የለም። ‘ጅሃድም ቢሆን?’ አሏቸው። እርሣቸውም ‘አዎን ጅሃድም ቢሆን ገንዘቡንና ነፍሱን ይዞ ወጥቶ ያልተመለሰ ሰው ብቻ ሲቀር።’ አሉ።” (ኢማም አህመድና ቱርሙዚ ዘግበውታል)

እንዲሁ በሌላ ዘገባም:-

لا تطفئوا سرجكم ليالي العشر

“በአሥርቱ ቀናት ለሊቶች ውስጥ መብራታችሁን አታጥፉ።” የሚል ዘገባ የመጣ ሲሆን ይህም ትርጉሙ “በነኚህ ቀናት ውስጥ ቁርዓን ቅሩ፣ በሰላትም በርትታችሁ ቁሙ ለማለት ነው” ተብሏል።

3. ዚክር ማብዛት

ከኢብኑ ዑመር (ረ.ዐ) እንደተዘገበው የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ አሉ:-