Get Mystery Box with random crypto!

ኤልሮኢ:( ትምህርት ) #ሰኔ_12_ለምን_በድምቀት_ይከበራል? #ሰኔ_12_ቅዱስ_ሚካኤል ቅድ | "ኤልሮኢ ዘተዋህዶ"

ኤልሮኢ:( ትምህርት )

#ሰኔ_12_ለምን_በድምቀት_ይከበራል?

#ሰኔ_12_ቅዱስ_ሚካኤል ቅድስት አፎምያ ያዳነበት ዕለት እንኻን አደረሳቹ የአመቱ ሰው ይበለን ታሪኩ እንዲህ ነውቅድስት አፎምያ ሀገሯ ኪልቅያ ነው፡፡ ባለቤቷ አስተራኒቆስ መስፍነ ኪልቅያ ነበረ፡፡ እርሷም በትዳር በነበረችባቸው ዘመናት እግዚአብሔርን ከሚወድ ባለቤቷ ጋር እግዚአብሔርን ስታገለግለው የኖረች ሴት ደገኛ ሴት ናት፡፡ በየወሩ በ29 ቀን የጌታችንን የልደቱን፣ ወር በገባ በ21 የእመቤታችንንና ወር በገባ በ12 የቅዱስ ሚካኤልን መታሰቢያ እያደረጉ ነዳያንን ይጎበኙ ነበር፡፡ ባለቤቷ አስተራኒቆስ ከዚህ ዓለም የሚያርፍበት ጊዜ እንደ ደረሰባወቀ ጊዜ ይሰጡት የነበረውን ምጽዋት እና የሦስቱን በዓላት መታሰቢያ ማድረግ እንዳታስታጉል ከአደራ ጋር አዘዛት፡፡ እርሷም የመልአኩን የቅዱስ ሚካኤልን ሥዕል ያሥልላት ዘንድ ባለቤቷን ጠይቃ አሠርቶ ሰጣት፡፡ በከበረ ቦታም አኖረችው፡፡ ባሏ ካረፈ በኋላ ያዘዛትን መንፈሳዊ ሥራ ከወትሮው አስበልጣ መሥራት ቀጠለች፡፡ ባሏም ታሞ ሞቶ ከሀብቷ ከንብረቷ እየሰጠች እየመጸወተች በጾም በጸሎት ተወስና ትኖር ነበር፡፡ ሰይጣን ለምቀኝነት አያርፍምና ደግ መነኩሴ መስሎ አጋንንትን መነኮሳይያት አስመስሎ መጥቶ ከደጅ ሆኖ አስጠራት፡፡
እርሷም "ከቤትገብታችሁ በቅዱስ ሚካኤል ሥዕል ፊት ጸልዩልኝ" አለቻቸው፡፡ ሰይጣናቱም "እኛማ በነግህ ጸልየናል?" አሏት፡፡ ቀጥሎም ሰይጣን."... እንደው አንቺ ግን ይህ ሁሉ ጾም ጸሎት ምን ያደርገልሻል? ሀብትሽን ሰጥተሸ መጨረስሽስ ስለምንድን ነው? በዚያ ላይ አንቺ ስትደክሚ የሚደግፍሽ ስታረጂ የሚጦርሽ ልጅ የለሽም ሁለተኛ ማግባት ኃጢአት መስሎሻልን? እነ አብርሃም እነ ዳዊት ከብዙ ሴቶች ብዙ ልጆች ወልደው የለምን? አሁንም ቤት ሰሪ ጎመን ዘሪ ልጅ ያስፈልግሻልና ባል አግቢ፣ እሺ በይኝ" አላት፡፡
ቅድስት አፎምያም "አባ ቆብህ መልካም ነበር ንግግርህ ግን ክፉ ነው፣ አትጹሚ አትጸልዩ ያልከኝ ጌታ ምጽዋት አበድር እመስዋዕት ብሎ የለምን? ሁለተኛ ባል አግቢ ማለትንስ ከምን አገኘኸው? እርግቦች እንኳን ባሎቻቸው ከሞቱባቸው ከሌላ ወንድ አይቀርቡም ታዲያ ጥንት በንጽሕና ሊኖር የተፈጠረ ሰው ሁለተኛ አላገባም ቢል ዕዳ ፍዳ ሊሆንበት ነውን?" ብላ ሞገተችው፡ የሰው ልጆች ጠላት የሆነው ሰይጣንም በመልካም አገልግሎት ስትበረታ አይቷታልና ዝም ብሎ ሊተዋት አልወደደም፡፡ ከላይ እንዳየነው ..በመጀመሪያ ባል ሳታገባ ማገልገሏን ትታ ሌላ ባል አግብታ ልጅ ወልዳ እንድትኖር በብዙ ማባበል ጠየቃት፡፡ ባሏ መንግሥተ ሰማያትን ስለወረሰ ምንም ምጽዋት እንደማይሻ አስመስሎ ነገራት፡፡ ቅድስት አፎምያ ግን ዳግመኛ ትዳር ላለመመሥረት ቃል ኪዳን እንደገባች ርግብንና ዖፈ መንጢጥን አብነት አድርጋ እነርሱ እንኳ በሕይወት ዘመናቸው ከአንድ ባል ውጪ ሌላ ባል እንደማያውቁ በመጥቀስ አሳቡን እንደማትቀበለው ገለጸችለት፡፡ ሰይጣንም አስመሳይ መሆኑ አላዋጣ ሲለው ማንነቱን ቀይሮ ሊያንቃት ቢሞክር የእግዚአብሔርንና የቅዱስ ሚካኤልን ስም ጠርታ አባረረችው፡፡ እርሱም ተመልሶ መጥቶ እንደሚያጠፋት ዝቶባት እንደአቧራ በኖ እንደ ጢስም ተኖ ጠፋ፡፡
በሰኔ 12 ቀን የቅዱስ ሚካኤልን መታሰቢያ እያዘጋጀች ሳለች ሰይጣን ብርሃናዊ መልአክ መስሎ መጣ፡፡ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል እንደሆነ ገልጾ የመጀመሪያውን የመሰለ ከንቱ ምክሩን አሰማምሮ አቀረበላት፡፡ አሳቡንም የእግዚአብሔር ፈቃድና አሳብ እንደሆነ አድር ለማሳመን ሞከረ፡፡ ሰይጣን አስቀድሞ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በገዳመ ቆሮንቶስ መጻሕፍትን እየጠቀሰ እንደተፈታተነው ሁሉ ቅድስት አፎምያንም ለማሳመንም አብርሃምን፣ ይስሐቅን፣ ያዕቆብን፣ ዳዊትን የመሳሰሉ ደጋግ አባቶችን ታሪክ እየጠቀሰ ወደ ትዳር እንድትገባ ደጋግሞ ወተወታት፡፡ ቅድስት አፎምያም በእግዚአብሔር ኃይል ጸንታበቅዱስ ሚካኤልም ተራዳኢነት ታምና "የእግዚአብሔር መልአክ ከሆንክ መንፈሳዊ ማረጋገጫህ የሆነው የመስቀል ምልክት የታለ?" በማለት በምድራዊ ንጉሥና በጭፍራው መካከል የሚኖርን የጋራ መግባቢያ መንገድ ዋቢ አድርጋ ጠየቀችው፡፡ ለጊዜው "በእኛ በመላእክት ዘንድ እንዲህ አይደለም" ብሎ ሊሸነግላትና አቋሟን ሊያስቀይራት ሞከረ። ከቤቷ ያለ የቅዱስ ሚካኤል ሥዕል ላይ ያለውን ምልክት አብራርታ የእርሱ ግን ከዛ ጋር አንድነት እንደሌለው አረጋገጠችበት፡፡ በመቀጠልም ከቤቷ ላለው ለቅዱስ ሚካኤል ሥዕል እጅ እንዲነሣ ጠየቀችው፡፡ በዚህ ጊዜ መልኩ ወደ ትክክለኛ ሰይጣናዊ ማንነቱ ተለወጠና ጨለማ ለብሶ እየዛተ አነቃት፡፡ ቅድስት አፎምያም የከበረ መልአክ ቅዱስ ሚካኤልን "ድረስልኝ" እያለች በጠራችው ጊዜ መልአኩም ፈጥኖ በመድረስ ከሰይጣን እጅ አዳናት፡፡ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልም ለሰይጣኑ ተገቢውን ቅጣት ሰጥቶ ቅድስት አፎምያን ባረካት፡፡ የዕረፍት ቀኗ በዚህ ቀን መሆኑን ነግሮ ቤቷን እንድታዘጋጅ አዘዛት፡፡ የበዓሉን ዝግጅት አከናውና ሥጋ ወደሙን ተቀብላ ኤጲስ ቆጶሱንና ካህናቱን እንደ የመዓርጋቸው ጠርታ በቤቷ አክብራ ተቀበለቻቸው፡፡ ለነዳያንና ለጾም አዳሪዎች በኤጲስ ቆጶሱና በካህናቱ እጅ ገንዘቧን መጽውታ መንገዷን አሳመረች፡፡ ስለ ኃጢአቷ እንዲጸልዩላት ተማፅና በፊታቸው ተንበርክካ ጸለየች፡፡ ባሏ ያሠራላትን የቅዱስ ሚካኤልን ሥዕል አቅፋ ስማ ከተማጸነች በኋላ ሰኔ 12 ቀን በሰላም ዐረፈች፡፡


@aleroe
ለሀሳብ አስተያየት @Aleroebot