ማቴዎስ 18 ¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯ ²¹ በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ ወደ እርሱ ቀርቦ፦ ጌታ ሆይ፥ ወንድሜ ቢበድለኝ ስንት ጊዜ ልተውለት? እስከ ሰባት ጊዜን? አለው። ²² ኢየሱስ እንዲህ አለው፦ እስከ ሰባ ጊዜ ሰባት እንጂ እስከ ሰባት ጊዜ አልልህም። ²³ ስለዚህ መንግሥተ ሰማያት ባሮቹን ሊቈጣጠር የወደደን ንጉሥ ትመስላለች። ²⁴ መቈጣጠርም በጀመረ ጊዜ፥ እልፍ መክሊት ዕዳ ያለበትን አንድ ሰው ወደ እርሱ አመጡ። ²⁵ የሚከፍለውም ቢያጣ፥ እርሱና ሚስቱ ልጆቹም ያለውም ሁሉ እንዲሸጥና ዕዳው እንዲከፈል ጌታው አዘዘ። ²⁶ ስለዚህ ባሪያው ወድቆ ሰገደለትና፦ ጌታ ሆይ፥ ታገሠኝ፥ ሁሉንም እከፍልሃለሁ አለው። ²⁷ የዚያም ባሪያ ጌታ አዘነለትና ለቀቀው፥ ዕዳውንም ተወለት። ²⁸ ነገር ግን ያ ባሪያ ወጥቶ ከባልንጀሮቹ ከባሮቹ መቶ ዲናር ዕዳ ያለበትን አንዱን አገኘና፦ ዕዳህን ክፈለኝ ብሎ ያዘና አነቀው። ²⁹ ስለዚህ ባልንጀራው ባሪያ ወድቆ፦ ታገሠኝ፥ ሁሉንም እከፍልሃለሁ ብሎ ለመነው። ³⁰ እርሱም አልወደደም፥ ግን ሄዶ ዕዳውን እስኪከፍል ድረስ በወኅኒ አኖረው። ³¹ ባልንጀሮቹ የሆኑ ባሮችም ያደረገውን አይተው እጅግ አዘኑ፥ መጥተውም የሆነውን ሁሉ ለጌታቸው ገለጡ። ³² ከዚያ ወዲያ ጌታው ጠርቶ፦ አንተ ክፉ ባሪያ፥ ስለ ለመንኸኝ ያን ዕዳ ሁሉ ተውሁልህ፤ ³³ እኔ እንደ ማርሁህ ባልንጀራህ የሆነውን ያን ባሪያ ልትምረው ለአንተስ አይገባህምን? አለው። ³⁴ ጌታውም ተቈጣና ዕዳውን ሁሉ እስኪከፍለው ድረስ ለሚሣቅዩት አሳልፎ ሰጠው። ³⁵ ከእናንተ እያንዳንዱ ወንድሙን ከልቡ ይቅር ካላለ፥ እንዲሁ ደግሞ የሰማዩ አባቴ ያደርግባችኋል። 374 views ✞ ⒷĩⓃⓄ ▬ , 18:47