Get Mystery Box with random crypto!

ለሀገርና ለማህበረሰብ በጎ ተግባር የፈጸሙ ሰዎችን የማመስገን ባህልን ማዳበር ይገባል -ፕሬዚዳንት | AMN-Addis Media Network

ለሀገርና ለማህበረሰብ በጎ ተግባር የፈጸሙ ሰዎችን የማመስገን ባህልን ማዳበር ይገባል -ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ

አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ነሐሴ 29 ቀን 2014

ኢትዮጵያውያን ለሀገርና ለማህበረሰብ በጎ ተግባር የፈጸሙ ሰዎችን የማመስገን ባህልን ሊያዳብሩ እንደሚገባቸው የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ።

10ኛው የበጎ ሰው ሽልማት መርሐግብር ዛሬ በአዲስ አበባ የተካሄደ ሲሆን ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ የዓመቱ ልዩ የበጎ ሰው ተሸላሚ ሆናለች።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ባስተላለፉት መልዕክት "በጎነት ለተወሰነ ግለሰብ፣ሃይማኖት፣ ባለሥልጣን ብቻ የተወሰነ ምግባርና ተግባር እንዳልሆነ ተናግረዋል።

በጎ ሰዎች ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች ሲተርፉ ነገ የተሻለ ይሆናል ያሉት ፕሬዚዳንቷ፤ ሁሉም ሰው ሥራውን በታማኝነት በመፈፀም በጎነትን በተግባር ሊያሳይ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ዛሬ በበጎ ሰው ሽልማት ስማቸው ከፍ ያሉ በጎ አድራጊዎች ታሪክ ለሌሎችም አርዓያ የሚሆን ነው ብለዋል።

በተለይም በዘንድሮ የበጎ ሰው ሽልማት አራት ሴቶች ተሸላሚ መሆናቸው የሴቶች ሚና ሀገራዊና ማህበረሰባዊ ሚና እያደገ መምጣቱን ያሳያል ነው ያሉት።

ለአብነትም የእነ ዶክተር ርብቃ ጌታቸው፣ የኮማንደር ደራርቱ ቱሉ ታሪክ ትልቅ ምስክር መሆኑን በማንሳት።

ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ሀገርና ህዝብን ያገለገሉ ኢትዮጵያውያንን የማመስገን ባህል ሊዳብር እንደሚገባም ተናግረዋል።

"በማኀበረሰባችን በአብዛኛው ሰዎችን የማመስገን እና የዕውቅና የመስጠት ንፉግነት አለብን" ያሉት ፕሬዘዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ በጎነትን ምንጊዜም ማበረታታት አለብን ብለዋል።

የበጎ ሰው ሽልማት መርሐ ግብር ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ በነበሩ ዓመታት ለ187 በጎ ሰዎችና ድርጅቶች እውቅና ሰጥቷል።

የመምህርነትን እና መንግስታዊ ሃላፊነትን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች ነው ሽልማቱ የሚሰጠው።

ኢዜአ እንደዘገበው ለዘንድሮው የበጎ ሰው ሽልማትም 691 እጩዎች ለዘርፎቹ ቀርበው፥ ለየዘርፎቹ የመጨረሻዎቹ እጩዎች ተለይተው ዛሬ ተሸላሚ ሆነዋል።

በጎ ሰሪዎችን እውቅና በመስጠት ሌሎች በጎዎችን መፍጠር ዓላማው ያደረገው ይህ መርሐግብር በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ለሀገር እና ለወገን መልካም ለሰሩ እና በጎ ለዋሉ ሽልማትና እውቅና የሚሰጥበት ነው።