Get Mystery Box with random crypto!

የትግራይን ህዝብ ለዳግም ጦርነት እየዳረገ ያለው አሸባሪው ሕወሓት እየፈፀመ ያለው ጥፋት፣ ህዝባዊ | AMN-Addis Media Network

የትግራይን ህዝብ ለዳግም ጦርነት እየዳረገ ያለው አሸባሪው ሕወሓት እየፈፀመ ያለው ጥፋት፣ ህዝባዊ ውግንና እንደሌለውና አሸባሪነቱን በተግባር ያረጋገጠ ነው-የመከላከያ ሚኒስትር

አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ነሐሴ 26 ቀን 2014

የትግራይን ህዝብ ወደ ዳግም ጦርነት ያስገባው አሸባሪው ሕወሓት ህዝባዊ ውግንና የሌለውና አሸባሪነቱን የሚያሳይ መሆኑን የመከላከያ ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሐም በላይ ተናገሩ።

ከሽብርና ጦርነት ውጭ ሌላ ህልውና የሌለው አሸባሪው ህወሃት ለ3ኛ ጊዜ የትግራይን ህዝብ ወደ ጦርነት ማስገባቱንም ገልጸዋል።

የመከላከያ ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሐም በላይ በመግለጫቸው የተዘረጋን የሰላም አማራጭ በመናቅ ሌላ ዙር ጦርነት ማወጁ የቡድኑ ተፈጥሯዊ ባህሪ ስለመሆኑ ጠቁመዋል።

ከትግራይ ህዝብ ጥያቄ በመፍራትና የሌሎች ፀረ ኢትዮጵያ ሃይሎችን ፍላጎት ለማሳካት በማለም ዳግም የጀመረው ጦርነት መሆኑንም ገልጸዋል።

አሸባሪው ህወሃት ከአፈጣጠሩ ጀምሮ የተለየ ሀሳብና አጀንዳ መቀበልና መስማት የማይሻ መሆኑን የሚናገሩት ዶክተር አብርሃም፤ የተለየ ሃሳብ ያለውን አካል እየገደለና እያስወገደ የመጣ ቡድን መሆኑን አስረድተዋል።

በንግግርና በሰላም አምኖ ችግር የፈታበት አንዳችም የታሪክ አጋጣሚ የለም ሲሉም ተናግረዋል ።

አሸባሪ ቡድኑ በቀሰቀሰው ጦርነት የትግራይ ህዝብ ክፉኛ መጎዳቱን አስታውሰው ህዝቡ ሰላም ባለማግኘቱ ጥያቄዎችን የማቅረብ እድል መነፈጉንም ይናገራሉ።

የትግራይ ህዝብ ሰላም ካገኘ በርካታ ጥያቄዎችን ያነሳል በሚል ስጋት የሰላም በሮችን በመዝጋት በጦርነት አማራጭ መቀጠሉን ገልጸዋል።

በዚህም ቡድኑ "ልጆቻችን የት አሉ" የሚለውን የክልሉን ህዝብ ጨምሮ በባለፈው ጦርነት ህዝቡ የደረሰበትን ጉዳት ስለሚጠይቅና ዕድሜዬ ያጥራል በማለት በስጋት ውስጥ ሆኖ እየፈፀመ ያለው ወንጀል መሆኑን ጠቅሰዋል።

በሌላ በኩል ጦርነቱ የትግራይ ህዝብ ሳይሆን የኢትዮጵያን አንድነትና ሰላም የማይፈለጉ ታሪካዊ ጠላቶች የቤት ስራን ተቀብሎ እየሰራበት ያለ ነው ብለዋል።

የትግራይ ህዝብ የጦርነትን አውዳሚነት በታሪኩ የተረዳ ሰላም ፈላጊ ህዝብ መሆኑን ገልጸው የጥፋት ቡድኑ ባለው ድብቅ ፍላጎት ሀሰተኛ ፕሮፓጋነዳ እየነዛ ህዝቡን ለሌላ ዕልቂት እየዳረገው መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም ሕወሓት የሀሰት ትርክትና ፕሮፖጋንዳ በመፍጠር የትግራይ ክልል ህዝብ ለዘመናት በሠላምና በአንድነት አብሮ ከኖረው መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ለመለያየት እየሰራ መሆኑን ነው ያስረዱት።

የሽብር ቡድኑ በሰሜን ዕዝ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት ከመፈጸሙ በፊት መንግሥት ረጅም እርቀት ተጉዞ የሠላም ጥረት ማድረጉንም ጠቅሰዋል።

አሁንም ቢሆም መንግሥት ለሠላም የዘረጋውን እጅ ሳያጥፍ ዘላቂ ሠላምና መረጋጋት እንዲመጣ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

መንግስት በተደጋጋሚ የሰላም አማራጭን ቢያቀርብም አሸባሪው ሕወሓት የሰላምን መንገድ በመዝጋት በጥፋት እንቅስቃሴው መቀጠሉን ገልጸዋል።

መንግስት የዘረጋውን የሰላም እጅ በመግፋት የትግራይን ህዝብ በማደናገርና በማስገደድ ወደ ሌላ ዙር ጦርነት ያስገባው ተጠያቂነት እንዳይኖር አጀንዳ ለመፍጠር እንደሆነም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በጀግንነቱ፣ በዲስፕሊኑና በህዝባዊነቱ የሚታወቅ ሰራዊት እንደሆነ ገልጸው፤ከለውጡ በኋላም ሰራዊቱ በዕውቀት፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ የሚመራና ኢትዮጵያን የሚመስል ሰራዊት ስለመገንባቱ ገልጸዋል።

የኢፌዴሪ የአገር መከላከያ ሠራዊት አሸባሪውን ሕወሓት ጨምሮ ከማንኛውም ወገን የሚሰነዘርን ጥቃት በብቃት መመከት በሚያስችል ቁመና ላይ የሚገኝ መሆኑንም ሚኒስትሩ ማረጋገጣቸውን ከኢዜአ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል ።