Get Mystery Box with random crypto!

8/ የዒዱል አድሓን እርድ ለመፈጸም የነየተ የአላህ ባሪያ (ወንድም ሆነ ሴት) ወሩ ከገባበት ጊዜ | የኡስታዝ አቡ ሀይደር ትምህርቶች ስብስብ

8/ የዒዱል አድሓን እርድ ለመፈጸም የነየተ የአላህ ባሪያ (ወንድም ሆነ ሴት) ወሩ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ፡- የሰውነት ጸጉሩን መላጨትም ሆነ መቀነስ፣ የእጁንም ሆነ የእግሩን ጥፍር ማስተካከል፣ ከገላው ላይ የተወሰነ ቆዳንም ቢሆን ቆርጦ ማንሳት አይፈቀድለትም፡፡ ይህ ብይን የሚመለከተው የዒዱን እርድ በራሱ ወጪ ለማረድ የነየተውን ግለሰብ ብቻ ነው፡፡ ቤተሰቦቹን ብይኑ አይመለከታቸውም፡፡

ሰውየው በቀጥታ እራሱም አራጅ ሆነ፡ ወይም በወኪል ቢያሳርድ ኃላፊው እሱ እስከሆነ ድረስ ብይኑ ይመለከተዋል፡፡ ወኪል ሆኖ የሚያርደውን ሰው ግን ብይኑ አይመለከተውም፡፡

ኡሙ ሰለማህ (ረዲየላሁ ዐንሃ) እንደነገረችን የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- "የዙል-ሒጃህን ጨረቃ ካያችሁና አንዳችሁም ኡድሑያን (እርድን) ከነየተ፡ ጸጉሩንና ጥፍሩን (ከመቀነስ) ይቆጠብ" (ሙስሊም 1977)፡፡

በሌላ ዘገባ ላይ ደግሞ ‹‹ከጸጉሩና ከሰውነቱ (ቆዳው) ይቆጠብ›› ይላል፡፡
ስለዚህ ዛሬ ዕለተ ቅዳሜ የዚል-ቂዕዳህ 29ኛው ቀን ስለሆነ፡ ወሩ በዚያው ሊጠናቀቅም ስለሚችል፡ የመግሪብ አዛን ከተሰማ በኋላ ያለው ምሽት የዙል-ሒጃህ 1ኛ ቀን ሆኖ ይጀምራል ማለት ነው፡፡ ወሩ ሠላሳ ከሞላ ደግሞ፡ ከእሁድ መግሪብ በኋላ ወሩ የዙል-ሒጃህ 1ኛ ቀን ይሆናል ማለት ነው፡፡ እናም ለዒዱ እርድን የነየታችሁ ወንድምና እህቶች ሆይ! ከዛሬ መግሪብ አዛን በፊት (የጸጉር፣ የጥፍርና የቆዳ) ጣጣችሁን ጨርሱ፡፡

ሌላው ሊታወቅ የሚገባው ነገር፡ እርዱን የነየተ ሰው፡ በዙል-ሒጃህ የመጀመሪያዎቹ ዘጠኝ ቀናት ውስጥ ጸጉሩን ወይም ጥፍሩን ቢቀንስ፡ ከፋራው ‹ካሳው› ተውበትና ኢስቲግፋር ብቻ ነው በማለት ዑለሞች ፈትዋ ሰጥተዋል (ኢብኑ ቁዳማህ፡ አል-ሙግኒይ 9/346)፡፡
አላህ ተጠቃሚ ያድርገን።

Click and Like ➤➤ https://www.facebook.com/Ustaz.Abuhyder
Join us ➤➤ http://t.me/abuhyder