Get Mystery Box with random crypto!

#የሸዋል ፆም ፍች (ትንሹ ዒድ) በአቡ ሀይደር በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነ | የኡስታዝ አቡ ሀይደር ትምህርቶች ስብስብ

#የሸዋል ፆም ፍች (ትንሹ ዒድ)
በአቡ ሀይደር
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ምስጋና የዓለማት ጌታ ለሆነው ለአላህ የተገባ ነው፡፡ የአላህ ውዳሴና ሰላም፡ የሰላም አለቃና መምህር ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ ይሁን፡፡ ድልና የበላይነት ሐቅን ለማንገስና ሀሰትን ለማርከስ፡ በደልን አጥፎቶ ፍትህን ለማስፈን ዕውቀታቸውን፣ ንብረታቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ጊዜያቸውንና ህይወታቸውን መስዋእት በማድረግ ለሚታገሉት የአላህ ባሮች ይሁን፡፡
በተወሰኑ (ሁለት ወይም ሶስት) ብሔሮች ዘንድ ከረመዷን ዒድ (ዒዱል-ፊጥር) ማግስት ጀምሮ ለተከታታይ ስድስት ቀናት የሸዋልን ጾም ይጾሙና ሰባተኛውን ቀን እንደ ዒድ ያከብሩታል፡፡ ምክንያቱን ጠይቄ ለማወቅ እንደሞከርኩት ይህን ይመስላል፡-
የዒዱል-ፊጥር ቀን ደብዘዝ ብሎ በደንብ ሳይሞቅ የምናሳልፈው ቀኑ አንድ ቀን ስለሆነና በነጋታው ተመልሰን ወደ ሸዋል ጾም ስለምንገባ ነው፡፡ ስለዚህ ባሉት ተከታታይ ስድስት ቀናት የሸዋልን ጾም በመጾም ሁለቱንም (ረመዷንንም ሸዋልንም) እንጨርስና ከሰባተኛው ቀን ጀምሮ በደንብ ዒዱን እናከብራለን፡፡ እንበላለን እንጠጣለን፡፡ ጎረቤት፣ ጓደኛ፣ ዘመድ እንጠይቃለን፡፡ ብዙ ቀናቶች አሉንና፡፡
ከዚህ ምክንያት መረዳት እንደሚቻለው ሰዎቹ የዒዱል-ፊጥር ቀን አንድ ቀን ብቻ በመሆኑ በሰፊው ለመብላትና ለመጠጣት፣ ከዘመድ አዝማድ ጋር ለመዘያየር የማይበቃ መሆኑ ነው እንጂ የሸዋል ዒድ አለ ብለን አይደለም የሚል ነው፡፡
ማስተካከያ፡-
1ኛ/ የኢስላም ሃይማኖት እንዳስተማረን ከሁለቱ ዒዶች (ዒዱል ፊጥር እና ዒዱል አድሓ) ውጪ፡ ሙስሊሞች ሌላ ዒድ የላቸውም፡፡ የአላህ መልክተኛ ከደነገጉት ውጪ አዲስ ስርአትን መደንገግ በሃይማኖቱ ላይ መጨመር ነው፡፡ ይህ ደግሞ ቢድዐ ይባላል፡፡ የሸዋል ወር 8ኛው ቀን የሸዋል ፆም መፍቻ ዒድ ቢሆን ኖሮ፡ በዒድ ቀን መፆም ሐራም ነውና በዚህ ቀን አትፁሙ የሚል ትእዛዝ በሐዲሥ በሰፈረ ነበር፡፡ ግን የለም፡፡
2ኛ/ የሸዋል መጀመሪያ ቀን ዒዱል ፊጥር መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ዒድ ደግሞ የመደሰቻ፣ የመብያና የማብያ፣ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት መለዋወጫ ቀን ነው፡፡ ግን በመጀመሪያው ቀን ብቻ ነው መብላትና ማብላት፣ መዘየርና መደሰት የሚቻለው ያለው ማነው? የሸዋልን ሁለተኛና ሶስተኛ ቀናትስ መብላትና ማብላት፣ መዘያየር አይቻልም? ይቻላል፡፡ ስለዚህ ከላይ የቀረበው ምክንያት አጥጋቢ አይደለም፡፡
3ኛ/ የሸዋል ስድስት ቀናት ጾም በመጀመሪያዎቹ የሸዋል ቀናቶች ላይ ብቻ የተገደበ አይደለም፡፡ ሸዋል ሙሉ አንድ ወር 29/30 ነው፡፡ ስለዚህ ከወሩ ውስጥ የሚመቸውን ቀን መርጦ በማከታተልም ሆነ በማፈራረቅ ሸዋልን መጾም ይቻላል፡፡ እናም የደስታውን ቀን ማርዘም የሚፈልግ ከዒዱል-ፊጥር በኋላ ያለውንም ቀን መጠቀም ይቻላል፡፡ በቀሩት ቀናት ደግሞ ሸዋልን መጀመር ይቻላል፡፡
4ኛ/ ከዒዱል-ፊጥር ማግስት ጀምሮ ያሉትን ተከታታይ ስድስት ቀናት የጾመ ቤተሰብ በቀጣዩ ቀን በመብላትና ቀኑን እንደ ዒድ ቆጥሮ ሲያሳልፈው፡ ከመሐከላቸው አንድ ሰው ጾሙን ባለመጨረሱ (ቀዷእ ቢኖርበት ወይም ዘግይቶ ቢጀምር) እነሱ የሚበሉበትን ቀን ቢጾመው የቤተሰቡ አካላት ይቃወሙታልን? በዒድ ቀን እንዴት ትበላለህ ይሉታልን? አዎ! ከሆነ ምላሹ፡ ሰዎቹ ቀኑን ዒድ አድርገው ይዘውታል ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ በዲነል-ኢስላም ላይ የተጨመረ ፈጠራ ‹‹ቢድዓህ›› ይባላል፡፡ አላህና መልክተኛው ከዒዱል-ፊጥር እና ከዒዱል አድሓ ውጪ የበዓል ቀን አልደነገጉልንም፡፡ የሸዋል ዒድ የሚባለው መሰረት የለውም እና እንደ-ዒድ አድርገው የሚይዙ ሰዎችን ቢድዓ መሆኑን ማስተማርና ማስገንዘብ ይጠበቅብናል፡፡
4. ሌላው ሊታወቅ የሚገባው ነገር ቢኖር፡- ከዒዱል ፊጥር ማግስት ጀምሮ በተከታታይ የሸዋልን ስድስት ቀናት የጾመ ሰው በቀጣዩ ቀን መብላት መጠጣት አይችልም ማለት አይደለም፡፡ ሰውየው ጾሙን እስካጠናቀቀ ድረስ መብላት መጠጣት ይችላል፡፡ ዋናው ነገር በቀኑ ላይ ሲበላም ሆነ ሲጠጣ ቀኑን ዒድ ነው ብሎ እንዳይመለከተውና እንደ-ዒድ አድርጎ እንዳይዘው ነው፡፡ የዒዱል-ፊጥር ቀንንም በአግባቡ ሊያከብረው ይገባል፡፡ ወላሁ አዕለም፡፡
Click and Like ➤➤ https://www.facebook.com/Ustaz.Abuhyder