Get Mystery Box with random crypto!

መልካም ብስራት ሼይኽ መሐመድ ሁሴን አል አሙዲ የአሳይታውን ፕሮጀክት ለማጠናቀቅ ቃል ገቡ በአፋር | Ustaz abubeker ahmed/ኡስታዝ አቡበከር አህመድ

መልካም ብስራት
ሼይኽ መሐመድ ሁሴን አል አሙዲ የአሳይታውን ፕሮጀክት ለማጠናቀቅ ቃል ገቡ

በአፋር ክልል በአሳይታ ከተማ በሼይኽ መሐመድ ሁሴን አል አሙዲ አማካኝነት ለአፋር ህዝብ ሙሉ ወጪውን በመሸፈን ታላቁን የሱልጣን አሊ ሚራህ ኢስላማዊ ማዕከል እና ሌሎች የልማት ስራዎች አስገንብቶ ለማስረከብ ወደ ስራ ተገብቶ የነበረ ቢሆንም እውቁ የሃገራችን ባለሃብት ሼይኽ መሐመድ ሁሴን አል አሙዲ ብዙ ገንዘባቸውን ውጪ ካደረጉ ቡኃላ በፖለቲካ አሻጥር ምክንያት በክልሉ እያካሄዱ ከነበሩት በርካታ የልማት ስራዎች ተገፍተው እንዲወጡ በማድረግ እና የዚህን ፕሮጀክት ፋይናንስ ማድረግ እንዲያቆሙ በመግፋት ግንባታው እና የልማት ስራዎች እንዲቆም መደረጉ ይታወሳል::

ሼይኽ መሐመድ በክልሉ በርካታ ኢንቨስትመንት እና የልማት ስራዎች በመስራት ህዝባቸውን እና መላው ሃገራቸውን ለመጥቀም ብዙ ቢንቀሳቀሱም በቀድሞ ስርኣት ከክልሉ ከሁሉም የልማት እንቅስቃሴያቸው ሙሉ ለሙሉ ተገፍተው እንዲወጡ ተደርገዋል::

ለሁለት አስርት አመታት ግንባታው የቆመው እና እሳቸው ያስጀመሩት ይህ ታላቅ ፕሮጀክት ዳግም ተጠናቆ ህዝቡን እና ሃገርን እንዲጠቅም ለማስቻል እንቅስቃሴ ሲደረግ የቆየ ሲሆን ከቀናት በፊትም ተቋሙ በሚገኝበት አሳይታ ከተማ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አቶ አወል እርሱን ጨምሮ የተለያዩ ታላላቅ ኡለሞች፣ዱዓቶች እና የክልል መጅሊስ አመራሮች የተካፈሉበት ታላቅ የገቢ ማሰባሰቢያ ተካሂዷል::

በዚህ ፕሮግራም ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አቶ አወል አርባ ፕሮጀክቱን ላስጀመሩት እና ከክልሉ በግፍ ተገፍተው እንዲወጡ ለተደረጉት ሼይኽ መሐመድ ሁሴን አል አሙዲ በይፋ ወደ ክልሉ ተመልሰው ለህዝባቸው ማድረግ የሚፈልጉትን የልማት ስራዎች ሁሉ ይሰሩ ዘንድ ሁኔታዎችን በሙሉ እንደሚያስተካክሉ ቃል በመግባት ጥሪ አድርገውላቸዋል::

ይህን ለአፋር ህዝብ እና ለሃገር የሚጠቅም ግዙፍ ተቋም የተፈጠሩ ችግሮችን በማስተካከል ዳግም ግንባታው ይጠናቀቅ ዘንድ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ የቀረበላቸው ሼይኽ መሐመድ ሁሴን አል አሙዲ ምንም እንኳን ከበርካታ የልማት ስራዎቻቸው በግፍ ተገፍተው እንዲወጡ ቢደረጉም ለህዝባቸው እና ለሃገራቸው ካላቸው ፍቅር እና መልካም እሳቤ የተነሳ የቀረበላቸው ጥሪ በመቀበል ፕሮጀክቱን ሙሉ ለሙሉ ለማጠናቀቅ ቃል መግባታቸውን በተወካያቸው አማካኝነት አሳውቀውኛል:: አልሐምዱሊሏህ

እኚህ ታላቅ ሃገር ወዳድ ባለሃብት ሃገራቸውም እና ህዝባቸውን ለመጥቀም ለልማት ሥራዎች ብዙ ገንዘባቸውን አፍስሰው በግፍ ተገፍተው እንዲወጡ ቢደረጉም ከህዝባቸው እና ሃገራቸው የሚበልጥባቸው ምንም እንደሌለ በማስመስከር ይህን ታላቅ ፕሮጀክት ለማጠናቀቅ ቃል በመግባታቸው በራሴ ስም ላቅ ያለ ምስጋናዬን ለማቅረብ እወዳለሁ

የህዝቡን ጥሪ ለሳቸው በማድረስ እና ሁኔታዎች እንዲመቻቹ በማድረግ ትልቁን ሚና ለተጫወተው ለሳቸው ተወካይ ወንድም ጀማል አህመድም ምስጋናዬ የላቀ ነው:: ወንድም ጀማል ሃገራዊ የልማት ፕሮጀክቶችንም ሆነ ሌሎች ኸይር ስራዎችን እሳቸው እንዲሳተፉበት በማድረግም ሆነ በግሉም በርካታ የኸይር ስራዎችን በመስራት ለማህበረሰቡም ለሃገርም ትልቅ አስተዋፅኦ እና ድጋፍ እያበረከተ ያለ ሃገር ወዳድ ወንድማችን ነው::

ሼይኽ መሐመድ አል አሙዲ ወደሚወዱት ሃገራቸው አላህ በሰላም እንዲመልሳቸው፣ መልካም ስራቸውን ሁሉ አላህ እንዲቀበላቸው፣ ለሃገራቸው እና ለህዝባቸውም ብዙ ማድረግ የሚፈልጉትን መልካም ስራ ሁሉ ለመስራት ይችሉ ዘንድ ረጅም እድሜ ከጤና ጋር ይወፍቃቸው ዘንድ ዱዓዬ ነው::

በተጨማሪም ይህ እንዲሳካ ላገዘን እና በርካታ የኸይር ስራዎች ላይ እየተሳተፈ ለሚገኘው የሳቸው ተወካይ ለሆነው ወንድም ጀማል አህመድም አላህ መልካም ስራውን ይቀበለው!