Get Mystery Box with random crypto!

እነጌታቸው ረዳ አዲስ አበባ እንዳሉ ይሰማል። ቅዳሜና እሁድ በዳውሮ ዞን ሃላላ ሎጅ እንደነበሩም ሹ | አቢሲኒያ - Times

እነጌታቸው ረዳ አዲስ አበባ እንዳሉ ይሰማል። ቅዳሜና እሁድ በዳውሮ ዞን ሃላላ ሎጅ እንደነበሩም ሹክ ተብለናል። ለሁለተኛ ጊዜ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ተገናኝተዋል። ከጥል በኋላ ፍቅር አይጣል ነው። ብልጽግና ሲደመር ህወሀት የቀድሞ ኢህአዴግ ሊሆን ዳርዳርታው ወደ መሀል እየመጣ ይመስላል። የባለፈው የሃላላው ግንኙነታቸው የፕሪቶሪያውንና የናይሮቢውን የስምምነት ወረቀቶች እንዲቀዳደዱና በሃላላው መዝገብ አዲስ ቃለመሃላ እንዲፈጽሙ ማድረጉን ማስተባበያ የሚያስፈልገው አይሆንም። የሃላላው ቃለመሀላ ስጋ ለብሶ ትግራይን እየመራት ነው። የእነጌታቸው የዚህኛው ዙር አመጣጥ ደግሞ ከፌደራሉ መንግስት የድርሻቸውን ስልጣን ለመዝገን እንደሆነ ይገመታል። በቅርቡ ሪፖርተር እንግሊዘኛው ላይ እንደተዘገበው አቶ ጌታቸው የፌደራል መንግስቱን ስልጣን ለመጋራት ከጠሚ/ሩ ጋር ንግግር መጀመሩን ገልጸዋል። ህወሀት በምን አይነት ቅርጽና መልክ ዳግም ወደስልጣን ማማው እየወጣ እንዳለ ግልጽ አይደለም። ህወሀት አብቅቶለታል ብላችሁ ለተዘናጋችሁ እንግዲያውስ እርማችሁን አውጡ። ይሄኛው ህወሀት ቂም በሆዱ ያረገዘ፡ ለበቀል ጥርሱን እያፏጨ ያለ፡ ከበፊት ጭካኔው መቶ እጥፍ ጨምሮ የሚመጣ ነው።
ህወሀት የጦርነት ሞተሩን እያሞቀው ነው። ፉከራ ቀረርቶው የያን ሰሞን፡ ምስራቅ አፍሪካ ላይ የሚችለን የለም አይነት ፕሮፖጋንዳውን ዳግም ጀምሮታል። የፈረደበት የትግራይ ወጣት ለሌላ ዙር ጦርነት ስልጠና እንዲገባ እየተደረገ ነው። ወልቃይት ዒላማ ተደርጋለች። ሰሞኑን ከወደወልቃይት ያነጋገርኳቸው የአከባቢው አመራሮች እንደሚሉት ህወሀቶች ''በቅርቡ በመዳፋችን ትገባላችሁ። አይቀርላችሁም'' እያሉ መልዕክት እንደሚልኩባቸው ገልጸውልኛል። ከዛቻና ፉከራው ባሻገር በቅርብ ርቀት ምሽግ እየማሱም እንደሆነ መረጃው እንዳላቸው አውግተውኛል። የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከመሀል ትግራይ ወጥቶ የህወሀት ሰራዊት ተረክቦታል። ይህ መሆኑ ለወልቃይቶች አይናቸውን ለአፍታም እንዳይከድኑ እንዳደረጋቸው ይናገራሉ። እንደአመጣጡ እንመልሰዋለን የሚለው ወኔ እንደእቶን እሳት ውስጣቸው ይንቀለቀላል። አልፈርድባቸውም። የሚያሳዝነው የወልቃይት ጉዳይ የእነሱ ብቻ ይመስል ሌላው በዝምታ ርቆ መቀመጡ ነው። የወልቃይት ጉዳይ የኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ ነው።
የፌደራል መንግስቱ በተለይም የኦሮሚያ ብልጽግና ከወልቃይት አንጻር አቋሙ በግልጽ ባይታወቅም ደምቀው የሚሰሙ ጭምጭምታዎች ግን ''ጉዳዩ የሁለት ክልሎች ነው። ፌደራል መንግስት ጣልቃ አይገባም'' አይነት እንደሆነ ያመላክታሉ። ባለፈው ጥር ወር መጀመሪያ ላይ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ያነጋገሩት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደህንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ይህቺን ሀሳብ አነሱና '' ጦርነቱ እኮ የግዛት ማስመለስ አይደለም'' የምትል ውስጠ ወይራ ንግግር ጣል አደረጉባት። ለሚገባው በደንብ ይገባዋል። እስከአሁንም ወልቃይቶች በጀት የተነፈጋቸው፡ የመሰረተ ልማት አውታሮች የራቋቸው፡ የትግራይ ከተሞች በመብራትና ኢንተርኔት ሲንበሸበሹ አሁን ድረስ የወልቃይት አከባቢ በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ እንዲሰነብት የተፈረደበት ስለምን ተብሎ እንደሆነ መጨረሻው እስኪነገረን መጠበቅ ያለብን አይመስለንም።
መጪው ጊዜ አጓጊና አስጨናቂ ነው። ህወሀቶች ወልቃይትን ለመሰልቀጥ ተዘጋጅተዋል። ፌደራል መንግስቱ አንድ ሱሪ አብረን እናጥልቅ በሚል ግንኙነት ከህወሀት ጋር በአዲስ ፍቅር ከንፏል። ነገ ከነገ ወዲያ ህወሀቶች አፈሙዛቸውን ወደወልቃይት ቢያዞሩ የፌደራል መንግስቱ ምን አቋም ሊወስድ ይችል ይሆን? በሁለት ክልሎች ጸብ አልገባም? በእርግጠኝነት ጠሚ/ሩ ስልጣናቸውና ቀጣይ ጉዞአቸው በወልቃይት ላይ በሚኖራቸው አቋም ላይ የሚወሰን ይሆናል። ወልቃይት ለእሳቸው እጣ ፈንታ የሪፈረንደም ያህል ተቀምጣለች።
messay mekonen
@abisiniya_times