Get Mystery Box with random crypto!

በስመ አብ፤ ወወልድ፤ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!! ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ | አቢሲኒያ - Times

በስመ አብ፤ ወወልድ፤ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ
በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ወቅታዊ ጉዳይ ከመንግሥት ጋር
እየተደረገ ስለሆነው ውይይት እና የካቲት ፭ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም
በሀገር አቀፍና በዓለም አቀፍ ደረጃ ሊደረግ ስለታሰበው ሰላማዊ ሰልፍ አስመክቶ የተሰጠ መግለጫ
ሮሜ ፭፤፫-፬ “ መከራ ትእግስትን እንዳያደርግ፤ ትእግስትም
ፈተናን፤ ፈተናም ተስፋን እንዳያደርግ እያወቅን በመከራችን
ደግሞ እንመካለን”

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን!
በመንፈስ ቅዱስ የሚመራው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ
ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በቅርቡ ከቤተ ክርስቲያናችን
ሃይማኖታዊ፤ ቀኖናዊ እና አስተዳደራዊ ሥርዓት ፍጹም ሕገ
ወጥ በሆነ መንገድ በመደራጀት የቤተ ክርስቲያንን መብትና
ጥቅም የጎዳ ተግባር መፈጸሙ ይታወሳል፡፡ የተከበረውን
የአበው ሐዋርያዊ ሢመተ ኤጲስ ቆጶስነት ሥርዓት
በመፈጸማቸው ምክንያት በተፈጠረው የቤተ ክርስቲያንን
ሉዓላዊ ክብርና ልዕልና የማቃለል፣ ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ
ውለታ የዘነጋ፣ ሕልውናዋን እና አንድነቷን ለመናድ የተደረገ
ከፍተኛ ጥቃት በመፈጸሙና መንግሥትም የቤተ
ክርስቲያናችንን ሕግና ሥርዓት፣ እንዲሁም ተቋማዊ ሕልውና
እንዳያስከብር እና እንዳያከብር በተደጋጋሚ ሲጠይቅ ቆይቷል፡፡

ከዚህም ውስጥ ቅዱስ ሲኖዶስ በየካቲት ፪ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም
ባወጣው መግለጫ መንግሥት በዚሁ አካሄድ ሕግ እየጣሰ እና የቤተ ክርስቲያኒቱን ክብር እና ልእልና እያዋረደ የሚቀጥል
ከሆነ ቤተ ክርስቲያን መንግሥት የጣሰውን ሕግ መሠረት
በማድረግ መብቷን ለማስከበር እስከ አሁን ድረስ ፍጹም
ሰላማዊ የሆነውን እንቅስቃሴዋን አድማሱን በማስፋት በየካቲት ፭ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም ለማድረግ ያቀደችውንና ያሳወቀችውን ሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ሰላማዊ ሰልፍ ያለማንም ከልካይነትበራሷ አደባባይ የምታከናውን መሆኑን ስታሳውቅ ቆይታለች፡፡

በዚሁ መሠረት መንግሥት ቅዱስ ሲኖዶስ በመግለጫው
የሰጠውን ቀነ ገደብ ከግምት ውስጥ በማስገባትና ጥሪውን
በመቀበል በየካቲት ፫ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም ለአስቸኳይ ውይይት
ዝግጁ መሆኑን በተመረጡ የሀገር ሽማግልዎች አማካኝነት
መልእክቱ ሲደርሰን ካለው ወቅታዊ የሰላም እና ጸጥታ ሁኔታ
አንጻር ጥሪውን በመቀበላችን በብፁዕ ወቅዱስፓትርያርክ
የተመራ አሥራ ሁለት ብፁዓን ሉቃነ ጳጳሳት ፣ የኢፌዴሪ
ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር፣
ሚኒስትሮች፣ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና የሀገር
ሽማግልዎች በተገኙበት ሰፊ ውይይት ተካሂዷል፡፡
በውይይቱም የተነሱት ነጥቦች በዋንኛነት ቤተ ክርስቲያን
ሃይማኖታዊ፤ ቀኖናዊ እና አስተዳደራዊ ሕግን መሠረት ባደረገ
መልኩ ጠብቃ የምትሠራ እና ከዚህ ውጭ ምንም አይነት
ድርድር የልለው መሆኑን ገልጻለች፡፡ በዚህም መነሻ መንግሥት የቤተ ክርስቲያንን አቋም በመቀበል ወደፊትም የቤተ ክርስቲያንን አንድነት እና ሉዓላዊነትን በጠበቀ መንገድ
እንደሚሠራ አረጋግጧል፡፡

በዚህ የፈተና ጊዜ ውስጥ የቅዱስ ሲኖዶስን መመሪያ በመቀበል ራስን የቤተ ክርስቲያን ሕልውና መስዋእት አድርጎ በማቅረብ፤ በክርስቶስ ደም የከበረችውን ቤተ ክርስቲያንን የመጠበቅ እና የማስጠበቅ ከጸጉር መላጨት እስከ ገመድ መታጠቅ በእንባና በዋይታ መላው ሕዝበ ክርስቲያን ሀዘናችሁን የገለጻችሁበት መንገድ የቤተ ክርስቲያን ሕልውና ማስጠበቅ መሠረት ሆኗል፡፡

በዚህም ሂደት ሕይወታቸውን በሰማእትነት፤ አካላችሁን ለአካል ጉዳት፤ ኑሯችሁን ለፈተና ፤ ለስደት፤ ለእንግልት እንዲሁም ለእስራት አሳልፋችሁ የሰጣችሁ ልጆቻችን ቅዱስ ሲኖዶስ ሁልጊዜም ውለታችሁን ሲያስታውስ የሚኖር ሲሆን የጉዳት ሰለባ ለሆኑቱም መንግሥት የድርጊቱን ፈጻሚዎች ለይቶ በሕግ አግባብ ተጠያቂ እንደሚያደርግ እና አሁን ላይ እስር፤ ወከባ፤ እንግልት እየተፈጸመባቸው ያለት ብፁዓን ሉቃነ ጳጳሳት፤ የሀገረ ስብከት ሠራተኞች፤ አገልጋይ ካህናት እና በተለያዩ አደረጃጀቶች የሚገኙ የቤተ ክርስቲያኒቱን ልጆች ችግሩ በአስቸኳይ እንዲቆምና የታሠሩትም እንዲፈቱ፤
አገልግልታቸውን በሰላምና በነጻነት መስጠት እንዲችሉ
ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡

በትናትናው እለት ከመንግሥት ጋር ባደረግነው ውይይት
መንግሥት የቤተ ክርስቲያኒቱን አቋም ሙሉ በሙሉ የተቀበለ
ቢሆንም ይህንን ለማስፈጸም የሚያስችል የአፈጻጸም የድርጊት ጊዜ የሚያስፈልግ በመሆኑ እሁድ የካቲት ፭ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም እንዲካሔድ የተወሰነው ሀገር ዓቀፍ እና ዓለም አቀፍ የአደባባይ ሰላማዊ ሰልፍ ለተወሰነ ጊዜ እንዲራዘም ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

በዚሁ እለትም ሕዝበ ክርስቲያኑ ሁለም በየአጥቢያችሁ
በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ዓውደ ምሕረት ላይ ባለመቅረት የተለመደውን የእለተ ሰንበት የሥርዓተ ቅዳሴ፤ የጸሎት፣ የምሕላ እና የትምህርተ ወንጌል ከወትሮው በተለየ የመንፈሳዊ ሥርዓት በማከናወን እንድታሳልፉ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡ የተከበራችሁ ውድ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን፤
ቅዱስ ሲኖዶስ በየካቲት ፭ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም የጠራውን ሀገር
አቀፍና ዓለም አቀፍ ሰላማዊ ሰልፍ ለተወሰኑ ቀናት
እንዲተላለፍ ያደረገው የአቋም ለውጥ አድርጎ ሳይሆን
አስቀድማ ቤተ ክርስቲያናችን በሮቿን ለሰላም ክፍት በማድረግ ባስተላለፈችው ጥሪ እና በአስቀመጠችው ቀነ ገደብ መሠረት በመንግሥት በኩል ወዲያውኑ ችግሩን ለመፍታት ፍላጎት በማሳየቱ ምክንያት ብቻ መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን፡፡ ነገር ግን መንግሥት የገባውን ቃል እና የወሰነውን ውሳኔ የማይፈጽም ከሆነ መንፈሳዊ ተጋድሏችን የሚቀጥል ይሆናል፡፡

ይህ ሂደት በባህሪው ረዥም ተጋድል እና ጽናት የሚጠይቅ
በመሆኑ እስከ አሁንም በፍጹም አንድነት እና መደማመጥ
የቅዱስ ሲኖዶሱን ድምጽ እየሰማችሁ በአንድነት እና በሕብረት እንደቆማችሁት ሁሉ ወደፊትም የቅዱስ ሲኖዶስን ድምጽ በትጋት እንድትጠብቁ እያሳሰብን በሕግ የተያዙት ጉዳዮችም የሕግ ሂደታቸውን ተከትለው የሚቀጥሉ መሆኑን እና እኛም በልዩ ሁኔታ የምናውቃቸው መሆኑን እንገልጻለን፡፡
መንግሥትም የቤተ ክርስቲያንን ጥሪ ተቀብሎ የውይይት
መድረክ በማዘጋጀት የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ በማክበር
በውሳኔው መሠረት የሚፈጸም መሆኑን ስላረጋገጠልን ቤተ
ክርስቲያን ታመሰግናለች፡፡

በተጨማሪም በዚህ የፈተና ወቅት በየደረጃው የምትገኙ በሀገር ውስጥ እና በመላው ዓለም የምትገኙ የቤተ ክርስቲያናችን የሥራ ኃላፊዎች፤ ሉቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፤ መነኮሳት፤ አገልጋይ ካህናት፤ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች፤ ልዩ ልዩ የቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊ ማህበራት እና መላው ምእመናንና ምዕመናት እንዲሁም ከቤተ ክርስቲያኗ ጎን የቆማችሁ እና አጋርነታችሁን የገለጻችሁ የሃይማኖትተቋማት፤ የሕግ ባለሙያዎች፤ ግለሰቦች፤ የማህበረሰብ አንቂዎች፤ የጥበብ ሰዎች፤ የሰብዓዊ መብት ተቋማት እና በዚህ ሂደት ውስጥ ድጋፍ ስትሰጡ የነበራችሁ የተለያዩ አካላት ቤተ ክርስቲያን እያመሠገነች ወደፊትም ልዩ ዕውቅና የምትሰጥ መሆኑን እናሳውቃለን፡፡

በመጨረሻም ቅዱስ ሲኖዶስ በጀመረው ፍጹም ሰላማዊ ና ሕጋዊ መንገድ ከመንግሥት ጋር የደረስንበትን ውጤት በየጊዜው የምናሳውቃችሁ ስለሆነ እንደዚህ ቀደሙ ፍፁም በሆነ መንፈሳዊ ጨዋነት የቅዱስ ሲኖዶስን መልእክት እንድትጠባበቁ፤ አሁንም ቢሆን ያለመዘናጋት ቤተ
ክርስቲያናችሁን በጥብቅ ሁኔታ እንድትጠብቁ እና ቤተ
ክርስቲያናችሁ ላይ የሚያጋጥሙትን ችግሮች ሁሉ በተዋረድ
ላለው መዋቅራችሁ እንድታሳውቁ አባታዊ መልእክታችንን
እናስተላልፋለን፡፡