Get Mystery Box with random crypto!

#ተግሣፅ_ዘቅዱስ_ኤፍሬም ሕይወትህን በአግባቡ መምራት ትፈልጋለህን? እንግዲያውስ ትሕትናን ተለማመ | የአብነት ትምህርት ቤት

#ተግሣፅ_ዘቅዱስ_ኤፍሬም

ሕይወትህን በአግባቡ መምራት ትፈልጋለህን? እንግዲያውስ ትሕትናን ተለማመድ፤ ያለ ትሕትና ተገቢውን ሕይወት መምራት አይቻልም፡፡ ሥራህን ሁሉ በመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ጀምር፡፡ ያን ጊዜ ፍሬዎችህ ወደ መንግሥተ ሰማያት ይደርሳሉ።

ሰው ከትሕትና ከራቀ ከትክክለኛው መንገድ ርቋል ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔርን የተወ ሰውን ርኵስ መንፈስ እንደ ሳውል ያስጨንቀዋል። የጠላት ወጥመድ በማር የተቀባ ነው፡፡ በማር ጣዕም የሚማረክ ሰው ሐዘንን ሁሉ በያዘ ወጥመድ ይያዛል። ትሕትናን ውደዱ፤ ያን ጊዜ ከሰይጣን ወጥመድ ውስጥ አትወድቁም፡፡ በትሕትና ክንፍ በበረራችሁ ቁጥር ሁል ጊዜ ከጠላት ወጥመድ በላይ ትሆናላችሁ።

ግልፍተኝነት እንደ በሰበሰ ረጅም ዛፍ ነው፤ ቅርጫፎቹ ሁሉ በቀላሉ የሚሰበሩ ናቸው᎓᎓ አንድ ሰው በወጣባቸው ጊዜ ከወጣበት ከፍታ ወዲያውኑ ይወድቃል፡፡ በመልካም ሐሳብ ልቡናው የበራ ሰው ግን ምስጉን ነው፤ ክብሩም ታላቅና ዘላለማዊ ነው።

እንግዲህ ራሳችንን ለመቆጣጠር እንጣር ያን ጊዜ ኃጢአታችንን እንረዳለን፡፡ ያን ጊዜም ሁል ጊዜ ራሳችንን ዝቅ እናደርጋለን፤ እንደ እባብ በእብሪት መወጠርን እና ራሳችንን ከፍ ከፍ ከማድረግ እንቆጠባለን፡፡ እንግዲህ ራሳችንን ዝቅ ዝቅ ማድረግን እንውደድ፤ በንጹሕ ልቡና ሆነን ምናልባት የተሰጠንን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ በኃጢአት ከማቆሸሽ እንታደግ ይሆናል።

መልካም ጸሎት በሳግ እና በዕንባ የታጀበ ነው፤ በተለይ ደግሞ በምሥጢር የሚፈስ ዕንባ፣ በልቡናው ከፍታ ሆኖ የሚጸልይ ጌታውን በፊቱ ያያል። እኛ የምንኖረውና የምንሔደው በእርሱ ፈቃድ ነውና። ልቡናችሁ ከጠነከረ በጌታችን ፊት አልቅሱ እርሱ የዕውቀትን ብርሃን ይገልጥላችኋል፤ ወደ እርሱ የሚወስዳችሁ አዲስ ልብንም ይሰጣችኋል።

ንስሓ የገቡና ምሕረት የለመኑ ሰዎች ዕዳቸው ተሰረዘላቸው፤ ነገር ግን ለሠራኸው በደል ምሕረት ስትለምን ወንጀልን እና በደልን፤ በወንድምህም ላይ ቂም መያዝን መተው ይገባሃል። ፍቅር ሳይኖርህ ወደ እግዚአብሔር የምታደርገው ልመና ከተዘጋው በር ውጭ ይቀራል፡፡ የጸሎትን በር የሚከፍት ፍቅር ብቻ ነው፡፡

ወንድምህን ብታስቀይም እግዚአብሐርን ታሳዝናለህ፤ ካንተ ጋር ካለው ከወንድምህ ጋር ሰላምን ከፈጠርህ ግን በሰማይ ካለው ከእግዚአብሔር ጋር ትታረቃለህ፡፡ ወንድምህን በፍቅር ብትቀበለው፣ በደሉንም ይቅር ካልከው እግዚአብሔርን ተቀበልክ፡፡

ስለዚህ በተናደዱ ሰዎች በኩል ከእግዚአብሔር ጋር ታረቅ፤ እንግዲህ የተበሳጩትን በማስደሰት እግዚአብሔርን አስደስተው፣ በታሰሩት ሰዎች በኩል እግዚአብሔርን ጎብኘው፣ በተራቡት ሰዎች በኩል እግዚአብሔርን አብላው፤ በታረዙ ሰዎች በኩል እግዚአብሔርን አልብሰው፣ መንገደኛን በመቀበል እግዚአብሔርን በአልጋህ ላይ አስተኛው፤ እግሮቹንም እጠበው፣ በማዕድህም አስቀምጠው፣ እንጀራህንም ከእርሱ ጋር ተካፈል፤ ጽዋህንም ስጠው᎓᎓ እርሱ ታላቅ ፍቅሩን አሳይቶሃልና፤ እርሱ ስለ አንተ ብሎ ትበላው ዘንድ ሥጋውን ቆርሶልሃል፣ ትጠጣው ዘንድም ደሙን አፍስሷል።

(#ድርሳነ_ቅዱስ_ኤፍሬም ገጽ 334 - 336 -በዲ/ን መዝገቡ ከፍያለው የተተረጎመ)

ለኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ልጆች
                •➢ ሼር // SHARE

  •✥• @abenet_tmhert •✥•
  •✥• @z_tewodros •✥•
✥ @abenet_tmhert •✥•            
  ✧━━━━━━━━━━━✧‌‌