ምናለ_ባይነጋ @ሀይማኖት_ንጉሴ (የዲማው) ይኼው ደሞ ነጋ፥ በስተ-ምስራቅ ወጣች፥የዘልማድ ፀሐይ፣ ለፍጡራን ሁሉ፥ ተስፋ ልትፈነጥቅ፥ ጨለማን ልትገልጥ፥ብርሃን ልታሳይ፣ ታዲያ ምነው ለኔ፥ ህመም ይዛ መጣች፥ከፍጡር ለይታ፣ ታንቺ ልብ ጋራ፥ አጥብቄ ያሰርኹትን፥ የፍቅር ሰንሰለት፥በጣጥሳ ልትፈታ፣ ይሻለኛል እኔ፥ ጭጋግ የወረሰው፥ ፅልመት የከበበው፥የሰማይ ማኩረፉ፣ ምን አለኝ ተቀኑ፥ ምን አለኝ ተንጋት፥ ደስታን ከሚሰጠኝ፥ ከትዝታሽ ጋራ፥መነጠል ነው ትርፉ፣ ሌሊቱ ምን ነስቶኝ፥ በጉጉት ናፍቄ ፥ምጠብቅ ጀምበሯን፣ መች አነሰኝ ለኔ፥ አንቺን ለማስታወስ፥ አትነጠቅ እንጂ፥ጨረቃ ማማሯን፣ ታስታውሰኛለች፥ ከጥቁሩ ሰማይ ላይ፥ ውበትሽን አያለሁ፥በጨረቃ በኩል፣ ነጫጭ ከዋክብትን፥ ታንቺ እያወዳደርኩ፥ አቻ እፈልጋለሁ፥ከጥርሶችሽ እኩል፣ እንዲህ ነው ማነጋው፥ ቁስሌን እያባበልኩ፥ የተከዳው ልቤን፥በትዝታሽ ስኩል፣ ነፋሱ ጠረንሽን፥ ጨረቃ መልክሽን፥ ሰማዩ ምስልሽን፥ አጉልቶ እየሳለ፥ ወደኔ ሲያመጣሽ፥አልለውም በቃኝ፣ ትዝታሽ ነውና፥ ታሸለበኝ እንቅልፍ፥ ተብቸኝነቴ፥ቀስቅሶ ሚያነቃኝ፣ ታዲያ ለምን ብዬ፥ ታንቺ ሚወስደኝን፥ጨለማውን ልርገም፣ ላመስግነው እንጂ፥ እድሜው እንዲበዛ፥ፀሎት መፃፍ ልድገም፣ መጥላትስ ንጋትን፥ መርገምስ ንጋትን፥ በቁስሌ ሽንቁር ስር፥ሻጣ እየሰደደ፣ ሰርክ እያሳመመኝ፥ ብቻዬን ሳወራ፥ በሀሜተኞች አፍ፥ያስባለኝ አበደ፣ መራገምስ ቀኑን፥ አንቺን ላያስረሳኝ፥ ከህይወት ማህደር፥ ክህደትሽን ብቻ፥ፊቴ እየጋረጠ፣ ሌቱ የቸረኝን፥ደስታ እያቋረጠ፣ ስጋን ለሚቦጭቅ፥ ለሀሜታም ምላስ፥ሰቶኝ አሳልፎ፣ ንጋት አይደለም ወይ፥ አበደ ያስባለኝ፥ ውሸታም መስካሪ፥ሰብስቦ አሰልፎ፣ ይህንን እየፃፍኩ፥ የብርሃን ፍላፃ ካይኔ ተተከለ፥ ክፍቱን በረሳሁት፥በመስኮቴ ታየኝ፣ የዘልማድ ፀሐይ፥ በስተምስራቅ ወጣች፥ ከትዝታሽ ጋራ፥ታንቺ ልትለየኝ፣ ጀምበር ዐይኗ ይጥፋ፥ በምዕራብ ስትጠልቅ፥ምስራቅ በሩን ይዝጋ፣ አሁን ምን ቸገረው?፥ ታንቺ ባይነጥለኝ፥ሌሊቱ ባይነጋ። 454 views𝑯𝒂𝒚𝒎𝒂𝒏𝒐𝒕 𝙽𝚒𝚐𝚞𝚜𝚒𝚎, 05:26